ኀብረተሰቡ ህዝባዊ በዓላት ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉ ሚናውን ሊወጣ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኀብረተሰቡ ህዝባዊ በዓላት ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉ ሚናውን ሊወጣ ይገባል
መስከረም 14/2015 /ኢዜአ/ ኀብረተሰቡ ህዝባዊ በዓላት ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጥሪ አቀረበ።
በኢትዮጵያ ያላትን በርካታ የማይዳሰሱ ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ 13 ቅርሶችን በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራን እንዳላት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከእነዚህ ቅርሶች ውስጥ አራቱ የማይዳሰሱ ቅርሶች ሲሆኑ፤ የመስቀል ዳመራ፣ የጥምቀት በዓል፣ የኦሮሞ ገዳ ስርዓት፣ የሲዳማ ህዝብ ዘመን መለወጫ "ፊቼ ጫምባላላ" በማይዳሰሱ የሰው ልጆች ወካይ ዓለም ዓቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ የማይዳሰሱ ቅርሶች አንጻር በርካታ ቅርሶችን ለማስመዝገብ መስራት እንደሚገባም ነው የተገለጸው፡፡
በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የማይዳሰሱ ቅርሶች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ እታገኝ አስረስ፤ ህዝባዊ በዓላት ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላላፉ ኀብረተሰቡ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ ነው የተናገሩት፡፡
ይህም በኢትዮጵያ ያሉ የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ባሻገር የተመዘገቡትን ጠብቆ ለማስቀጠል ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
የማይዳሰሱ ቅርሶችን ጠብቆ ማስቀጠል ካልተቻለ ከዓለም ቅርስነት መዝገብ ሊሰረዙ እንደሚችሉም ነው ያብራሩት፡፡
ባለስልጣኑ የወላይታ ዘመን መለወጫ “ጊፋታ” እና በሐረሪ ማኀበረሰብ በድምቀት የሚከበረውን ሸዋል ኢድን ጨምሮ በርካታ የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየሰራ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በዚህም የማይዳሰሱ ቅርሶችን የመጠበቅ፣የመመዝገብና የማልማት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቅርሶችን በዩኒስኮ ማስመዝገብ በቀላሉ በማስተዋወቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እንደሚጠቅም ገልጸው፤ በዘርፉ በአቅም ግንባታና ቅርስ ጥበቃ መስኮች የእውቀትና ክህሎት ሽግግር ለማድረግ እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡
አደጋ የተደቀነባቸውን ቅርሶች ለመጠበቅና ለመንከባከብ የሚያግዝ የፋይናስ አቅም ለመፍጠር እንደሚያግዝም እንዲሁ፡፡
ኢትዮጵያ ከማይዳሰሱ ቅርሶች ባሻገር ከአክሱም ሐውልቶች እስከ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ድረስ የተዘረጉ እና በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡ በርካታ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች አሏት።