"ጊፋታ" እና "ያሆዴ" የዘመን መለወጫ በዓላት በተለያዩ መርሀግብሮች እየተከበሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
"ጊፋታ" እና "ያሆዴ" የዘመን መለወጫ በዓላት በተለያዩ መርሀግብሮች እየተከበሩ ነው

ሶዶ እና ሆሳዕና (ኢዜአ) መስከረም 14 / 2015---የወላይታ እና የሀዲያ ብሔሮች የዘመን መለወጫ በዓላት "ጊፋታ" እና "ያሆዴ" በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድምቀት እየተከበሩ ነው።
የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነው ”ጊፋታ” ዛሬ ማለዳ በሶዶ ከተማ መከበር የጀመረው "ለጊፋታ እንሩጥ" በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደ የሩጫ ውድድር ነው።
“ጊፋታ” በብሔሩ ዘንድ ከአሮጌው ዓመት ወደአዲሱ መሸጋገርን የሚበሰርበት፤ ከአሮጌው ዓመት ጥንካሬና ድክመት ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑም ተገልጿል።
በተጨማሪም በዓሉ ሰላም፣ አንድነትና አብሮነትን በማጠናከር ረገድ ያለው ትውፊታዊ ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ነው የተመላከተው።
በአሁኑ ወቅት የ”ጊፋታ” በዓል የተለያዩ ብሔረሰቦች ተወካዮችና የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት በተለያዩ መርሃ ግብሮች በሶዶ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።

ለበዓሉ ተብሎ በተዘጋጀ ሲምፖዚየምም የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣ የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ለማ ገዙሜን ጨምሮ የየብሔረሰቦች ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በስነ ስርዓቱ ላይ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞትዮስን ጨምሮ ከፌዴራልና ከተለያዩ ክልሎችም የተወከሉ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ታድመዋል።
እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የሴቶችና ወጣቶች ተወካዮች መሳተፋቸው ታውቋል።
በመድረኩ ላይ የሲዳማ እና የወላይታ ብሔር ተወካዮች አንድነታቸውን የሚያሳይ ትርኢት አቅርበዋል።
የበዓሉ አከባበር በተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ውይይት በማድረግና አውደርዕይን በመጎብኘት ቀጥሎ እንደሚውል ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ ዜና የሀድያ ብሔር የዘመን መለወጫ የሆነው- "ያሆዴ" በዓል በሆሳዕና ከተማ "ሀድይ ነፈራ" በተባለ የበዓሉ ማክበሪያ ስፍራ በደማቅ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል'
በዓሉ በቅርብና በሩቅ ያሉ ተሰባስበው በጋራና በአንድነት የሚያከብሩት በመሆኑ ከብሔሩ ተወላጆች በተጨማሪ ከአጎራባች ዞኖችና ክልል የመጡ እንግዶች በታደሙበት በተለያዩ መርሃግብሮችም እየተከበረ ነው።
በዓሉ የብሔሩ ባህላዊ ትውፊት መገለጫ በሆነው የአባቶች ምረቃት እንዲሁም ውዝዋዜ እና የቁንጅና ውድድር ጨምሮ በልዩ ልዩ ኩነቶች እየተከበረ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጀላ መርዳሳ፣ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬን ጨምሮ ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች እና በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተገኝተዋል።

በተጨማሪም ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የወጣቶችና የሴቶች ተወካዮች ታድመዋል።