የአሸባሪዎች ጥቃት የኢትዮጵያን ብልፅግና ከማረጋገጥ አያስቆመንም- የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
የአሸባሪዎች ጥቃት የኢትዮጵያን ብልፅግና ከማረጋገጥ አያስቆመንም- የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት

መስከረም 14 ቀን 2015(ኢዜአ) የአሸባሪዎች ጥቃት የኢትዮጵያን ብልፅግና ከማረጋገጥ አያስቆመንም ሲል የመንግስት ኮምኒኬሽን አገልግሎት በወቅታቂ ጉዳዮች ዙርያ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ከሰሞኑ አሸባሪው ሸኔ ሆሮጉድሩ ወለጋ በንጹሐንና ዜጎችና በአካባቢው ሚሊሻ አባላት ላይ ግድያ ፈጽሟል ሲል አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።
በተለያዩ የምዕራብ ኦሮምያ አካባቢዎች በጸጥታ ኃይሎችና በሕዝቡ ቅንጅት ርምጃ የተወሰደበት ይህ አሸባሪ ቡድን እየተበተነ ወደ ሆሮ ጉድሩ ጃርደጋ ጃርቴ አካባቢ ሲሸሽ እንደነበር ታውቋል ነው ያለው።
አሸባሪው ሸኔ ይሄንን ግድያ በንጹሐን ላይ የወሰደው በሁለት ምክንያቶች መሆኑ ታውቋል ሲልም አስገንዝቧል።
የመጀመሪያው በትናንትናው ዕለት የተደመሰሱበትን ጃል ኡርጂ የተባለውን የአካባቢውን የሸኔ አዛዥና ጀሌዎቹን ደም ለመበቀል ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የመስቀልንና የኢሬቻን በዓላት ከወዲሁ ለማወክ ነው ብሏል በመግለጫው።
በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው አካባቢውን ከአሸባሪው ሸኔ በማፅዳት ላይ ይገኛሉ ሲልም አመልክቷል።
ታሪካዊ ጠላቶቻችን በተለያዩ ቦታዎች ዓላማቸው ሲሰናከልባቸው በንጹሐን ላይ የሚፈጽሙት የጭካኔ ድርጊት እጅግ አሳዛኝ ነው ሲል የገለጸው መግለጫው" ሆኖም ይህ የአሸባሪዎች የጥፋት እርምጃ የኢትዮጵያን ብልጽግና ከማረጋገጥ ሊያስቆመን አይችልም" በማለት አስታውቋል።