"ጊፋታ"-የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ የ3 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ተካሄደ

185

ሶዶ (ኢዜአ) መስከረም 14/2015 የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል የሆነውን "ጊፋታ" ምክንያት በማድረግ በወላይታ ሶዶ ከተማ የ3 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ተካሄደ።

በብሔሩ ነገ በድምቀት የሚከበረውን ጊፋታ- ዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ "ለጊፋታ እንሩጥ" በሚል መሪ ሀሳብ በተዘጋጀው የሩጫ ውድድር ላይ በወንዶችና በሴቶች ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች መሳተፋቸው ታውቋል።  

የአሮጌው ዓመት መገባደጃ እና የአዲሱ ዓመት ዋዜማን ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀው ታላቅ የ"ጊፋታ" በዓል የሩጫ ውድድር መሆኑም ተመላክቷል።

መነሻውን በከተማው ባለው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ ሕንጻ ፊት ለፊት ያደረገ ይህ የሩጫ ውድድር የከተማዋን የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚያካልል ታውቋል።

በወንዶችና በሴቶች ተከፋፍሎ በተካሄደው ሩጫ ለሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች የገንዘብ ሽልማት እና የምስክር ወረቀት መዘጋጀቱን የሩጫው አስተባባሪ ኮሚቴ አስታውቋል።

በዚህ ሩጫ ከ20 ሺህ በላይ ተወዳዳሪዎች መሳተፋቸው ታውቋል።

ውድድሩን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ለማን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተው በይፋ አስጀምረዋል።

አስተዳዳሪው በእዚህ ጊዜ እደገለጹት፣ ጊፋታ ከአሮጌው ወደአዲሱ ዓመት መሸጋገርን የሚያበስር በዓል መሆኑን ተናግረዋል።

"ጊፋታ በመተሳሰብ፣ በጋራ እና በአብሮነት ያለምንም ልዩነት የሚከበር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል" ብለዋል።

ለበዓሉ ከሚደረጉ ክዋኔዎች አንዱ በተለያየ ዘርፍ የተሳካላቸው ሲወደሱ፤ የደከሙት እንዲበረቱና ለቀጣይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ይበረታታሉ።

ከእዚህ በተጨማሪ በዓሉ በሌሎች ማህበራዊ ጨዋታዎችና ክዋኔዎች የሚከበር መሆኑ አብሮነትን ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

የ"ጊፋታ"ን በዓል ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው በእዚህ የሩጫ ውድድር ከተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ የስፖርት ቤተሰቦች፣ ስመጥር የሆኑ አትሌቶች፣ ከሲዳማ ክልልና አጎራባች ዞኖች የተውጣጡ ተወካዮች እንዲሁም የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች መሳታቻው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም