የደሴ ከተማ አስተዳደር በእሳት ቃጠሎ የወደሙ 18 መኖሪያ ቤቶችን መልሶ ገንብቶ ለተጠቃሚዎች አስተላለፈ

ደሴ ኢዜአ መስከረም 13/2015.. በደሴ ከተማ አስተዳደር ከአራት ወር በፊት አጋጥሞ በነበረው የእሳት ቃጠሎ የወደሙ 18 መኖሪያ ቤቶችን መልሶ ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ዛሬ አስተላለፈ።

በደሴ ከተማ በአራዳ ክፍለ ከተማ  ግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም በተከሰተ ድንገተኛ የእሳት አደጋ 18 መኖሪያ ቤቶች እና አራት የንግድ ቤቶች መውደማቸውን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በርክክቡ ስነስርዓቱ ላይ ገልጸዋል፡፡

ቃጠሎው በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱንና የከተማ አስተዳደርም በቃጠሎው የወደሙ ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ቃል ገብቶ እንደነበር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስታውሰዋል።

በዚሁ መሰረት የከተማ አስተዳደሩ በ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በቃጠሎው የወደሙ መኖሪያ ቤቶችን መልሶ በመገንባት በቃጠሎው ቤታቸው የወደመባቸው ወገኖች እንዲረከቡ ማደረጉን ተናግረዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ አቅም በፈቀደ ሁሉ መኖሪያ ቤት ለወደመባቸው ወገኖች የቤት ውስጥ ቁሳቁስ እንዲሟላላቸው በሚችለው አቅም እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ ለአራቱ ንግድ ቤቶች መስሪያ የሚሆን የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

ከተጋገዝን፣ ከተባበርን የማናልፈው ፈተና፣ የማንሻገረው ችግር የለም ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አሸባሪው ህወሓት የከፈተብንን ጦርነትም በጋራ መመከት ይኖርብናል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ህብረተሰቡ ደጀንነቱን በተግባር ከማረጋገጥ ባለፈ ጎን ለጎን የተጀመሩ ልማቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንዲተጋም አሳስበዋል፡፡

ከተጠቃሚ ግለሰቦች መካከልም አቶ ሀይሌ በለጠ በሰጡት አስተያየት በወቅቱ በተከሰተው የእሳት ቃጠሎ ቤታቸው ከእነ ሙሉ ንብረቱ መውደሙን ገልጸዋል፡፡

አክለውም በዚህም አምስት ቤተሰብ ይዘው ለችግር ተጋልጠው መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ከተማ አስተዳደሩ በተሻለ ደረጃ መልሶ ገንብቶ በማስረከቡም ምስጋና አቅርበዋል።

የቤት ውስጥ መጠቀሚያ ቁሳቁሱም በህብረተሰቡ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሆነ ገልፀዋል።

በርክክብ ስነ ስርዓቱ የደሴ ከተማ አመራሮች፣ ተጠቃሚ ግለሰቦችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም