ኢትዮጵያ ያሏትን ባህል እና እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት ለቅርሶች ጥበቃ እና እንክብካቤ ማድረግ ይገባል

መስከረም 13/2015/ኢዜአ/ ኢትዮጵያ ያሏትን መልካም ባህል እና እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሚዳሰሱ እና ለማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ እና እንክብካቤ ሊያደርግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር በመሆን መስቀል ደመራ "ለአንድነትና ሰላም" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ውይይት አካሂዷል።

የቢሮው   ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ ኢትዮጵያ የመስቀል ደመራን፣ የገዳ ስርዓትን፣ የፊቼ ጨምበላላና የጥምቀት በዓልን በዓለም የቅርስ መዝገብ በማይዳሰሱ የቅርስ ዘርፍ ማስመዝገቧን አስታውሰዋል።

እነዚህ ክብረ በዓላት በሃይማኖታዊና በባህላዊ ስርዓታቸው  መሰረት ቅርስነታቸውን በሚያስቀጥል መልኩ እየተከበሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመስቀል ደመራ በዓልን የዓለም የማይዳሰስ ቅርስነቱንና ኢትዮጵያዊ እሴቱን ጠብቆ ለማክበር በአዲስ አበባ ዝግጅት የተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዓሉን በአንድነት እንዲያከበረው ጥሪ አድርገዋል፡፡

በዓሉ ሲከበር መልካም እሴቶችን በማጉላት አንድነትን እና ሰላምን በኢትዮጵያዊያን መካከል ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ መሆን ይገባዋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለጹት የመስቀል በዓል በኢትዮጵያና በዓለም ህዝብ ተቀባይነት የሚኖረው ትክክለኛ ትውፊቱን ጠብቆ ሲከበር ነው።

የመስቀል በዓልንም በአግባቡ በማክበር ለመጪው ትውልድ በትክክለኛው መንገድ ለማስተላለፍ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በዓሉን በይቅርታ፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በመከባበር ማክበር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም