ቀጥታ፡

ለመከላከያ ሠራዊት የሚደረገው የደጀንነት ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል-የደቡብ ኦሞ ዞን

ጂንካ መስከረም 13 ቀን 2015 (ኢዜአ) የደቡብ ኦሞ ዞን ለመከላከያ ሠራዊት የሚደረገውን የደጀንነት ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ተካልኝ ጋሎ ተናገሩ።

የዞኑ ነዋሪዎቹ በሕግ ማስከበር ዘመቻ ላይ ለተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት  ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የቁም እንስሳትና የደረቅ ምግብ ድጋፍ እንዲሁም አሸባሪው ሕወሓትን የሚያወግዝ ህዝባዊ ሰልፍ ዛሬ አካሂደዋል ።

የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ተካልኝ ጋሎ እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት መንግስት በተደጋጋሚ የሰጠውን የሰላም እድል እንደ ሽንፈት በመቁጠር ራሱን ጀብደኛ እና ሌሎችን ደግሞ ደካማ አድርጎ በተደጋጋሚ የጦርነት ነጋሪት ሲጎስም ነበር።

ካለጦርነትና ግጭት ሊኖር የማይችለው የሽብር ቡድን የተዘረጋለትን የሰላም አማራጭ  አሻፈረኝ በማለት ጦርነት መክፈቱን ተናግረዋል።

''መንግስት ለሰላም የዘረጋው እጅ መቼም ቢሆን አይታጠፍም'' ያሉት አቶ ተካልኝ፤ የሰላማዊ አማራጭን በመግፋት ሀገር ለማፍረስ የተነሳን የሽብር ቡድን በመመከት የህዝብን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ዞኑ ለመከላከያ ሠራዊት የሚደረገውን  የደጀንነት ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠው፤ በዛሬው ዕለትም 7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የቁም እንስሳትና የደረቅ ምግብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

የዞኑ ህዝብ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመቆም የሚያደርገውን የደጀንነት ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው ፤የሽብር ቡድኑ የጠናከረ አንድነታችንን ለመሸርሸር በሚነዛው ፕሮፖጋንዳ ሳንሸበር ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን በማጠናከር የሽብር ቡድኑን ጥቃት  ልንመክት ይገባል ብለዋል።

''አባቶቻችን በጋሻና በጦር መስዋዕትነት ከፍለው ያቆዩትን ሀገር በተባበረ ክንዳችን አጽንተን ለትውልዱ እናሸጋግራለን'' ብለዋል።

 የዞኑ ህዝብ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ በማጠናከር ከሠራዊቱ ጎን መቆሙን በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

ዛሬ የተደረገው ድጋፍም ከዞኑ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ መንግስት ሠራተኞች፣ የንግዱ ማህበረሰብና ነዋሪዎች የተሰበሰበ መሆኑ አስታውቀዋል።

በህዝባዊ ሰልፉ ከተሳተፉት ነዋሪዎች መካከል  የጂንካ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ እመቤት ኃይለማርያም፤ በአሸባሪው ህወሓት የመከፋፈል ሴራ ህብረተሰቡ እንደማይታለል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ለሽብር ቡድኑ ተደጋጋሚ የሰላም አማራጭ ቢያቀርብም የሽብር ቡድኑ አለመቀበሉን ገልጸው፤ሰላም ከማይፈልግና ሰይጣናዊ አስተሳሰብ ከሚያራምድ ቡድን ጋር ህብረት መኖር እንደሌለበት ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ ሀገርን በመራበት 27 አመታት የሰራው ግፍ አልበቃ ብሎት ዳግመኛ ሀገርን ለማፍረስ የሚያደርገው እኩይ ሥራ የሚወገዝ ነው ያሉት ደግሞ ሌላዋ የህዝባዊ ሰልፉ ተሳታፊ ወይዘሮ ሰላምነሽ ልንገርህ  ናቸው።

''ኢትዮጵያዊያን አንድ ነን''ያሉት ወይዘሮ ሰላምነሽ፤ አንድነታችንን ለሚከፋፍሉ ለውስጥና የውጭ ጠላቶቻችን አንንበረከክም ብለዋል።

የደቡብ ኦሞ ህዝብ  ዛሬ ለ3ኛ ዙር በተደረገው የሀብት አሰባሰብ መርሃ ግብር  ከ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው 165 በሬዎች ፣274 የበግና የፍየል ሙኩቶች፣ 167 ኩንታል ደረቅ ምግብ እና  219 ደርዘን የታሸገ ውሃ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም