የውጭ ኃይሎች ጫና እያደረጉ ያሉት መንግስት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ቁርጠኛ አቋም በመያዙ ነው-- ዶክተር ዘለቀ ተመስገን - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ኃይሎች ጫና እያደረጉ ያሉት መንግስት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ቁርጠኛ አቋም በመያዙ ነው-- ዶክተር ዘለቀ ተመስገን
መስከረም 13/2015 (ኢዜአ) የውጭ ኃይሎች ጫና እያደረጉ ያሉት መንግስት የኢትዮጵያንና የህዝቧን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ቁርጠኛ አቋም በመያዙ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የሕግ አማካሪና የአፈጉባኤ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ዘለቀ ተመስገን ገለፁ።
የተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን ሰሞኑን ኢትዮጵያን በሚመለከት ያወጣው ሪፖርትም አንድ ጫና የማድረጊያ ፖለቲካዊ መሳሪያ መሆኑን ተናግረዋል።
ሪፖርቱ ሙያዊ ግዴታዎችን ያላሟላ ለአንድ ወገን ብቻ ያደላ መሆኑን ለኢዜአ የተናገሩት ዶክተር ዘለቀ መሬት ላይ ያሉ እውነታዎችን የካደ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሸባሪው ህወሓት በጭና፣ ማይካድራ፣ጋሊኮማ እና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የደረሱ ጥፋቶችን ያላከተተ መሆኑ ለአንድ ወገን ያደላና ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለመጫን ያለመ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
ምርመራው መሰረታዊ የምርምራ እሳቤዎችንና ዘዴን ያልተከተለ ከመሆኑም በተጨማሪ ገለልተኝነት የጎደለው መሆኑን ገልጸዋል።
ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ፖለቲካዊ ጫና ለማባባስ ያለመ ግብ መያዙንም እንዲሁ።
የሪፖርቱ የመጨረሻ ግብ የኢትዮጵያን እጅ በመጠምዘዝ የሚፈልጉትን ተላላኪ መንግስት ለማስቀመጥ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የመነጨ መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ ዓይነቱ በሰብዓዊ መብት ምርምራ ሽፋን ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን የማስፈጸም ተልዕኮን ኢትዮጵያውያን ፈፅሞ የሚያወግዙት መሆኑን በመጥቀስ።
የዚህ ሁሉ ጫና መነሻ ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹንና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ቁርጠኛ በመሆኑና እጁን የሚጠመዝዝ ተላላኪ መንግስት ባለመሆኑ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ጠንካራ መንግስትና ሀገር እንዳይኖር ካስፈለገ የሚደረገውን ጫና ለመቀልበስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ የሚጠበቅበትን የዜግነት ግዴታ መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ለማስቀጠል ውስጣዊ አንድነትን ከመቼውም ጊዜ በላይ በማጠናከር የውጭ ጫናውን መቋቋም የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።