ቀጥታ፡

ኢሬቻ የሰላምና አንድነት ምሳሌነቱ ተጠብቆ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት

መስከረም 13/2014 (ኢዜአ) ኢሬቻ የሰላምና አንድነት ምሳሌነቱ ተጠብቆ እንዲከበር ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት አባገዳዎች አሳሰቡ።

የዘንድሮ ኢሬቻ በዓል መስከረም 21 እና 22 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ እንደሚከበር ታውቋል።

በዚሁ መነሻነት በኦሮሚያ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በሚዘጋጀው 'ጉሚ በላል' የተሰኘ የውይይት መድረክ ''ኢሬቻ፤ የሰላም ምሳሌ፤ የእርቅና የወንድማማችነት በዓል'' በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት ተካሄዷል።

የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት አባገዳዎችና የባህል ተመራማሪዎች፤ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ማንነቱ የሚገልጽበት ነው ብለዋል።

ኢሬቻ ሰላም፣ አንድነትና ወንድማማችነት በተግባር የሚታይበት የአደባባይ በዓል መሆኑን ነው የተናገሩት።

በተለይ የኦሮሞ አባገዳዎች እንደተናገሩት የዘንድሮ ኢሬቻ በዓለም ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ሰላምና አንድነት በሚታይበት መንገድ መከበር አለበት ብለዋል።

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ በአገር ውስጥ ይሁኑ ከአገር ውጪ ያሉ ዜጎች ኢሬቻ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከበር እገዛ ሊያደርጉ ይገባልም ነው ያሉት።

በተጨማሪም ኢሬቻ የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተራራቀ የሚገናኝበት የኦሮሞ ታላቅ በዓል መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህም በመሆኑ ማንኛውም ሰው በዓሉ ላይ ሲሳተፍ በዓሉ የእሱ መሆኑን አውቆ የባህሉን እሴት መጠበቅ አለበትም ብለዋል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ በበኩላቸው የኢሬቻ በዓል መከበር የኦሮሞ ሕዝብ  አንድነት እንዲጠናከር እያደረገ መምጣቱን አንስተዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የኢሬቻ በዓል ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ያለውን መስተጋብር እንዲጎለብት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ መልካም ነገር የማይወጣላቸው አንድንድ ሀይሎች ኢሬቻን የፖለቲካ ማራመጃና የብጥብጥ ሜዳ ለማድረግ ይፈልጋሉ ብለዋል።

እነዚህ አካላት ይህን ካላደረጉ መኖር እንደማይችሉ የተናገሩት ኃላፊው የዘንድሮ ኢሬቻ በተለመደው መልኩ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ሁሉም መተባባር እንዳለበት አሳስበዋል። 

የኢሬቻ በዓል ከአዲስ አበባ 'ሆራ ፊንፊኔ'ና ከቢሾፍቱ 'ሆራ አርሰዲ' ባሻገር በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚከበር ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም