ቀጥታ፡

የተሻሻለው የአካቶ ትምህርት ስትራቴጂ በዚህ ዓመት ተግባራዊ ይሆናል-ትምህርት ሚኒስቴር

መስከረም 13/2015/ኢዜአ/ ከአስር ዓመታት በኋላ የተሻሻለው የልዩ ፍላጎት ወይም አካቶ ትምህርት ስትራቴጂ በዚህ ዓመት ተግባራዊ እንደሚሆን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስቴር ሶስተኛውን ሀገር አቀፍ የልዩ ፍላጎት(አካቶ) ትምህርት ጉባኤ በአዲስ አበባ   አካሂዷል።

በጉባኤው ላይ በፍትሐዊነትና አካታችነት ላይ አተኩሮ ከአስር ዓመታት በኋላ የተሻሻለው የአካቶ ትምህርት ስትራቴጂ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ስትራቴጂው ጥራትና ተገቢነቱን የጠበቀ የትምህርት እና ስልጠና አገልግሎት ተጠቃሚነት መብት ለሁሉም ልዩ የትምህርት ፍላጎት ላላቸው ዜጎች ለማረጋገጥ ዓላማ ያደረገ ነው።

ሁለት እጇ ላይ የአካል ጉዳት ያለባት ተማሪ ኬሪያ ጀማል የእጇን ተግባር በእግሯ እያከናወነች 11ኛ ክፍል ደርሳለች።

መጻፍ፣ መመገብ፣ ስራ መስራትና ሌሎች ተግባራትን በሁለት እግሮቿ እያከናወነች በትምህርቷ ውጤታማ ከሚባሉ ተማሪዎች ውስጥ አንዷ መሆኗን ተናግራለች።

የአካል ጉዳተኝነት ልክ እንደማንኛውም ዜጋ ተምሮ ውጤታማ ከመሆን እንደማያግድ በመግለጽ የሚያስፈልጋትን ድጋፍ ጠይቃለች።

በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎት ትምህርት ባለሙያ አቶ አለማየሁ ወልደቂርቆስ ባለፉት 10 ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የአካቶ ትምህርት ስትራቴጂ ልዩ የትምህርት ፍላጎት ያላቸው ዜጎችን ውጤታማ ለማድረግ ትኩረት አድርጎ መሻሻሉን ገልጸዋል።

ስትራቴጂው ለቀጣይ ስምንት ዓመታት ከ2015 እስከ 2022 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን እንደ ኬሪያ አይነት ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ተማሪዎችን ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው ብለዋል።

መንግስት የአካል ጉዳት ያለባቸው ህጻናት እንደማንኛውም ዜጋ ተገቢውን ትምህርት እንዲያገኙ ሁኔታዎችን በማመቻቸት አምራች ዜጎች እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም እንዲሁ።

በቀጣይ ሁለት ዓመታት 600 የድጋፍ መስጫ ማዕከላትን ለማቋቋም ከተያዘው እቅድ ውሰጥ በዚህ ዓመት 300 ለማቋቋም እየተሰራ ነው ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት ለአካል ጉዳተኞች ትምህርት በተሰጠው ትኩረት ለውጦች መምጣታቸውን ገልጸዋል።

አካል ጉዳተኞች ያላቸውን ችሎታ ተጠቅመው ለአገራቸው ልማትና ብልጽግና አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን አካል ጉዳተኛ ህጻናት ውስጥ በአንደኛ ደረጃ የትምህርት እድል እያገኙ ያሉት 8 በመቶ ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

በቅድመ መደበኛ 1 ነጥብ 7 በመቶ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ 2 ነጥብ 5 በመቶ ሲሆን አሁንም ወደ ትምህርት ገበታ መምጣት ያለባቸው ህጻናት በርካታ መሆናቸውን በጉባኤ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም