የሃይማኖት አባቶች ኢትዮጵያን ለማጽናትና በነፃነት ለማቆም የቀደሙ አባቶችን ታሪክ መድገም ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሃይማኖት አባቶች ኢትዮጵያን ለማጽናትና በነፃነት ለማቆም የቀደሙ አባቶችን ታሪክ መድገም ይጠበቅባቸዋል
መስከረም 13/2014 (ኢዜአ)የሃይማኖት አባቶችና ምዕመናኑ የኢትዮጵያን ህልውና ለማጽናትና በነፃነት ለማቆም የቀደሙ አባቶችን ታሪክ ዘመኑን በዋጀ መልኩ መድገም ይጠበቅብናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ ለዘመናት በጋራ ቆመዋል፤ የአሁኑ ትውልድም ይህንን ታሪክ ማስቀጠል እንዳለበት የሃይማኖት አባቶቹ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቅርስ ጥበቃና ቤተ- መፃህፍት ወመዘክር መምሪያ ዋና ኃላፊ መላከ ሰላም ቆሞስ ዶክተር አባ ቃለጽድቅ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለጹት ቤተክርስቲያኗ በየትኛውም አገራዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት በመሳተፍ ኃላፊነቷን እየተወጣች ትገኛለች።
ኢትዮጵያን ለመውረር የሚመጡ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሉዓላዊነቷን ለመሸራረፍ በጋራ መሰለፋቸውን አስረድተዋል።
ይህንን ተከትሎ የውጭ ወራሪ ኃይሎችን በመመከት ረገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባቶች ህዝቡን በማስተባበር የማይተካ ሚና እንደነበራቸው በመጠቆም።
ይህም ወራሪ ጠላትን በጋራ ከመመከት ባሻገር የሃይማኖት መሪዎችም ህዝባቸውንና ሀገራቸውን የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንደተወጡ ያሳዩበት መሆኑን ነው አባ ቃለጽድቅ ያብራሩት።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው በአድዋ ጦርነት የሁሉም ተጋድሎ አገርን ማዳን እንጂ የማንነት ጉዳይ አለመሆኑን አስታውሰዋል።
በወቅቱ አባታቸው ጭምር በውጊያው ተሳትፈው እንደነበር አስታውሰው የክርስትና እና የእስልምና አባቶች በጋራ ጠላትን ሲመክቱ እንደነበር በታሪክ መዝገብ ላይ መስፈሩን ጠቅሰዋል።
አገርን በእውነት ላይ ተመርኩዞ ከወራሪ ጠላት ለመጠበቅና ለማዳን እስከ ሞት ድረስ መዋደቅ በእስልምና እምነት ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውና በፈጣሪ ዘንድም የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
ይህም የሃይማኖት መሪዎች የእምነቱን አስተምህሮ ከማስተማርና ከመምራት ባሻገር የአገርን ዳር ድንበር፣ የዜጎችን ደህንነትና ሰላም የመጠበቅ ግዴታም እንዳለባቸው ነው ፕሬዝዳንቱ ያብራሩት።
የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሃፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ እንዲሁ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት የማይገባትን ጦርነት እንድትጋፈጥ መገደዷን ተናግረዋል።
አሁን የተከሰተውን የእርስ በእርስ ግጭት መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ የምዕራባውያን አጀንዳ ማስፈጸሚያ እንዳትሆን የሃይማኖት አባቶች በትጋት ሲሰሩ እንደነበርም አንስተዋል።
በተለይም የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች በመነጠል የራስን የፖለቲካ ፍላጎት ለማሟላት ይደረግ የነበረው ጥረት ትክክል አለመሆኑን ለማስገንዘብ በትኩረት ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ አሸባሪው ቡድን ከራሱ ህዝብ ይልቅ የምዕራባውያኑን ዓላማ በማስቀደሙና የአባቶችን ተግሳጽና ምክር ለመስማት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ንጹሃን ዜጎችን ለመከራ ዳርጓል።
የሃይማኖት መሪዎች ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው በጋራ የተማጸኑት ይህ ሁሉ መከራ እንዳይመጣና ህዝባቸውንም የመጠበቅ ሃላፊነት ጭምር ስላለባቸው ነው ብለዋል።
የየትኛውም እምነት ተከታይና ምዕመኑ የሰላም መሳሪያ በመሆን አገሩን መጠበቅ አለበት ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የምዕመናን ፣የወጣቶች መምሪያ ዳይሬክተር የላዛሪስት ማህበር ካህን አባ አብነት አበበ ናቸው።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአንድነት የሚኖሩባት አገር መሆኗን ተከትሎ ይህንን መልካም እሴት ለመሸርሸር የውስጥና የውጭ ጠላቶች በየጊዜው ትንኮሳ እንደሚያደረጉ ይናገራሉ።
በዚህም ከሃይማኖት መሪዎች ጨምሮ መላው ኢትዮጵያዊ አገሩን ለመጠበቅ የተሰለፈው ጦርነትን በመፈለግ ሳይሆን አገሩን ስለሚወድና ድንበሩን የመጠበቅ ሃላፊነት ስላለበት ነው ይላሉ።
በአገር ላይ የተደቀኑ ሁለንተናዊ ችግሮችና ፈተናዎች ሲያጋጥሙ የሃይማኖት አባቶች መፍትሔ ለማበጀት በኃላፊነት መስራታቸው የሰርክ ተግባራቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
ለዚህም ደግሞ ህዝቡ የራሱን ብሎም የአገሩን ሰላም ለማስጠበቅ በቅድሚያ ራሱ የሰላም መሳሪያ መሆን ይጠበቅበታል ብለዋል።