ኢትዮጵያ የምትሳተፍበት የታዳጊ አገራትና የባህር በር የሌላቸው አገራት ከፍተኛ ጉባኤ በኒውዮርክ እየተካሄደ ነው

967

መስከረም 13 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 77ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን ኢትዮጵያ ተሳትፎ የምታደርግበት የታዳጊ አገራትና የባህር በር የሌላቸው አገራት ከፍተኛ የምክክር መድረክ በኒውዮርክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ አገራቱ ችግሮችን በትብብርና በመደጋገፍ መፍታት በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

የበለጠ ትብብርን ለማበረታታትና የጋራ ዘላቂ ልማት ለማሳካት የንግድና የትራንስፖርት እንቅፋቶችን ለመቀነስ ቃል የገቡ ሲሆን፤ የቡድኑ አባል ኢትዮጵያ በውይይቱ ንቁ ተሳትፎ እያደረገች ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያን አቋም ያቀረቡት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ አየለ ሊሬ የባህር በር የሌላቸው አገራት በኮቪድ -19፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በምግብ፣ በኢነርጂ እና ፋይናንስ ቀውስ እየተፈተኑ ነው ብለዋል።

አገራቱ እያጋጠማቸው ያለውን ችግር ለመፍታት ከአሁን በፊት የተቀመጠውን የዶሃ ፕሮግራም ትግበራ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የዶሃ የትግበራ ፕሮግራም ፈጣን ለሆነ ዘላቂና አካታች የማገገሚያና ማቋቋሚያ መንገዶች ትኩረት መስጠቱን ታበረታታለች ነው ያሉት።

የዶሃ የትግበራ ፕሮግራም በመተማመንና እውነተኛ ቁርጠኝነት በማሳየት ከልማት አጋሮቻችን ጋር መተግበር ይገባዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈች ቢሆንም ከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነት በማሳየት የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ አዘጋጅታ በድህነት ቅነሳ፣ ስራ ፈጠራ፣ መዋቅራዊ ለውጥ፣ ሰላም እና መልካም አስተዳደርን ለማሻሻል እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ችግር ለመከላከልም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን በመተግበር 25 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን መናገራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም