አሸባሪው ህወሓት ዘመን ተሻጋሪ የህዝቦችን አብሮነት አደጋ ላይ ለመጣል ሲሰራ ቆይቷል -የፖለቲካ ፓርቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
አሸባሪው ህወሓት ዘመን ተሻጋሪ የህዝቦችን አብሮነት አደጋ ላይ ለመጣል ሲሰራ ቆይቷል -የፖለቲካ ፓርቲዎች
ሰመራ መስከረም 13/ 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን ከምስረታው ጀምሮ የህዝቦችን አብሮነት አደጋ ላይ ለመጣል ሴራ ይዞ ሲሰራ የቆየ ነው ሲሉ በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አስታወቁ።
የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሀንፈሬ መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ከምስረታው ጀምሮ በሴራና ክፋት የተጸነሰ ሃላፊነት የማይሰማው ነው።
ቡድኑ በሰልጣን ቆይታው ህዝብና ህዝብን በተለያዩ የሀሰት ትርክቶች እያናከሰ ሀገር ሲዘርፍና ከዚያም አለፍ ሲል የህዝቦችን የቆየ አብሮነትና አንድነት አደጋ ላይ ለመጣል ሴራ ሲሸርብ የኖረ መሆኑን ጠቁመዋል ።
"አሸባሪው ቡድን አብሮት የቆየው ክፋትና ሴራ አለቀው ብሎት በጥፋት ላይ ጥፋት እንዲሁም በወንጀል ላይ ወንጀል እየደረበ መቃብር ሊገባ እያጣጣረ ይገኛል" ብለዋል።
ቡድኑ በተለይም ባለፉት አመታት በአፋርና አማራ አጎራባች ህዝቦች ላይ የፈጸመው የግፍ፣ ግድያ፣ ዘረፍና ጾታዊ ጥቃት የእውነተኛ ማንነቱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
"አሸባሪው ቡድን በደምና በታሪክ ጥብቅ ትስስር ያላቸውን የትግራይ ህዝብን ከወንድሞቹ የአፋርና አማራ ህዝቦች ጋር ማብቂያ ወደ ሌሌው ግጭት ውስጥ በማስገባት እድሜውን ለማራዘም የማይሳካ ሙከራ አድርጓል" ብለዋል።
"ይሁንና ህዝቡ የአሸባሪ ቡድኑን ሴራ ጠንቅቆ የሚያውቅ በመሆኑ ዛሬም የአፋርና ትግራይ ህዝብ እንዲሁም የአማራና ትግራይ ህዝብ የሽብር ቡድኑን እኩይ ሴራ እያለፉ አብረው በሰላም እየኖሩ ነው" ሲሉ አክለዋል ።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ፊትም አንድነቱን በማጠናከር የቡድኑን አብሮነትን በመናድ ሀገር የማፍረስ ሴራ ሊያከሽፍ እንደሚገባ አቶ ሀንፈሬ አስገንዝበዋል።
"አሸባሪው የህወሓት ቡድን የህዝቦችን ዘመን ተሻጋሪ አብሮነትና ወንድማማችነት ለማጠልሸት የፈጸመው አሳፋሪ ተግባር ታሪክ ይቅር የማይለው ነው" ያሉት ደግሞ የአፋር ህዝብ ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መሀመድ ዳውድ ናቸው ።
"ቡድኑ ከተቻለ የስልጣን ፍላጎቱን በጉልበት ለማሳካት፣ ካልሆነ ደግሞ የህዝቦችን አብሮነት በማጠልሸት ሃገር ለመበተን ከኢትዮጵያዊ እሴት በእጅጉ ባፈነገጠ ሁኔታ ወንድማዊ አብሮነትና አንድነትን የሚጎዱ ሃላፊነት የጎደላቸው በርካታ ጸያፍ ተግባራት ፈጽሟል" ሲሉ አክለዋል።
"አሸባሪው ቡድን በአፋርና አማራ ክልሎች በወረራ በያዛቸው እንደ ጋሊኮማ፣ ማይካድራና፣ ጭናን በመሳሰሉ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የፈጸመው የግፍ ጭፍጨፋ የፍላጎቱና የሴራው ማሳያ ነው" ሲሉም አመልክተዋል ።
"ይሁንና ህዝቡ የሽብር ቡድኑን ከንቱ ሴራ በሆደ ሰፊነትና በብልጠት በማለፍ እንዲሁም እኩይ አላማውን በማክሸፍ ፍላጎቱ አንደማይሳካ አሳይቶታል" ብለዋል።
የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር ምክትል ሊቀመንበር አቶ መሀመድ አወል ወግሪስ በበኩላቸው እንዳሉት አሸባሪው የህወሓት ቡድን መንግስት ያቀረበለትን የሰላም አማራጭ ወደ ጎን በመተው በአጉል ትምህክት የከፈተው ጦርነቱ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ባህሪውን በግልጽ ያሳየ ነው።
ይኽው የቡድኑ ድርጊት ሲፈጠር ጀምሮ ችግሮችን በውይይትና በእውቀት የመፍታት ባህል የሌለው የአምባገነኖች ስብስብ መሆኑን ጭምር ያሰየ ነው" ብለዋል።
ቡድኑ በጦርነቱ ያሰበውን ማሳካት እንደማይችል ሲገነዘብ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገብቶ በየደረሰበት ንጹሃን ዜጎችን በግፍ ከመጨፍጨፍና ህብረተሰቡ የሚጠቀምባቸውን ተቋማት ከማውደም አልፎ እንስሳትን ሳይቀር በጥይት በመግደል ኢትዮጵያዊ አብሮነትን አደጋ ላይ ለመጣል መሞከሩን አመልክተዋል።
ህዝቡ አንድነቱን ከመቼውም በላይ በማጠናከር የቡድኑን እኩይ ሴራ ለመጨረሻ ጊዜ ሊያከሽፍ እንደሚገባ አቶ መሀመድ አስገንዝበዋል።