ቀጥታ፡

የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል የኢትዮጵያን የልማት ጉዞና ሉዓላዊነት ላይ አደጋ የሚደቅኑ ኃይሎችን መመከት በሚያስችል ዝግጁነት ላይ ይገኛል-ኮሎኔል ዓለማየሁ ሙለታ

መስከረም 13/2015  (ኢዜአ)  የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል የኢትዮጵያን የልማት ጉዞና ሉዓላዊነት ላይ አደጋ የሚደቅኑ ኃይሎችን መመከት በሚያስችል ሙሉ ዝግጁነት ላይ እንደሚገኝ የሪፐብሊካን ጥበቃ ኃይል አዛዥ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ዓለማየሁ ሙለታ ተናገሩ ።

ኮሎኔል ዓለማየሁ ሙለታ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሪብሊኩ ጥበቃ ኃይል በ2010 ዓ.ም ሲቋቋም የኢትዮጵያን ህልውና በሚያስጠብቅ መልኩ መገንባቱን ተናግረዋል።

የአሸባሪው ህወሃት በሰሜን እዝ አባላት ላይ የክህደት ጥቃት መፍጸሙን ተከትሎም የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል የአገርን ሉዓላዊነትና ህልውና በማስጠበቅ ረገድ የበኩሉን ሚና ተወጥቷል ነው ያሉት፡፡

በዚህም የሪፐብሊኩ ጥበቃ ኃይል ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን አሸባሪው ህወሃት ደቅኖት የነበረውን የሀገር ህልውና ስጋት እንዲከሽፍ ሚናውን መወጣቱን አንስተዋል፡፡

ሠራዊቱ አሁንም ኢትዮጵያ ሰላሟና ሉዓላዊነቷ ተከብሮ እንዲቀጥል አኩሪ ተግባር እየፈጸመ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በልማትና በብልፅግና ጉዞ ላይ እንደምትገኝ የገለጹት ኮሎኔል ዓለማየሁ፤ ለዚህ ጉዞ መሳካት የህዝቡ በሰላም ወጥቶ መግባት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ  የሪፐብሊኩ ጥበቃ ሃይል ሰላምና ደህንነትን በማስከበር ረገድ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሪፐብሊኩ ጥበቃ ሃይል የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የከፍታ ጉዞ በሚጻረሩ ሃይሎችን መመከት በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም