የኢትዮጵያን ቡና በቻይና ገበያ በስፋት ለማስተዋወቅ የሚያስችል የመግባቢያ ሥምምነት ተፈረመ

124

መስከረም 13/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ቡና ለቻይና ገበያ የሚያቀርበው “ለቡና” የተሰኘው ኩባንያ ሺያዎካሺያ ከተባለ የቻይና ዲጂታል የገበያ ማስተዋወቂያ ኩባንያ ጋር በትብብር ለመሥራት ሥምምነት ተፈራርሟል።

ሥምምነትቱን በቻይና “ለቡና” የተሰኘው ኩባንያ ተወካይ ካንግ ሺያኦሺያና እና የቻይና ዲጂታል ማስተዋወቂያ ኩባንያ ተወካይ ሺ ሚንግ ፈርመውታል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ሥምምነቱ የሁለቱ አገራትን የንግድ ግንኙነት ያጠናክራል።

የኢትዮጵያ ቡናን በቻይና ገበያ በስፋት ለማስተዋወቅና አገሪቱ ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

በተለይም ቻይና በኢንተርኔት የታገዘ ግብይት በመጠቀም ከ50 በመቶ በላይ የሆነውን የአገሪቱ ሽያጭ እንደምታከናውን በመጠቆም ሥምምነቱ የኢትዮጵያን ቡና በቻይና ገበያ ተደራሽ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።  

ቴክኖሎጂው በአጭር ጊዜ ውስጥ የግብይት መረጃውን በአንድ ጊዜ ለበርካታ ተጠቃሚ ማዳረስ የሚያስችል በመሆኑ ገበያውን በማሳለጥ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ፤ ኢትዮጵያ እሴት የተጨመረበት ቡናን በጥራትና በብዛት ማቅረብ ከቻለች የገበያ እድሉ  ለዘርፉ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው እምነታቸውን ገልጸዋል።  

ጎን ለጎንም ኢትዮጵያ የኢ-ኮሜርስ ግብይትን በመጠቀም የተለያዩ ምርቶቿን ለዓለም ገበያ እያቀረበች መሆኗን በመጠቆም።

ለአብነትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሊባባ በተሰኘው በኢንተርኔት የታገዘ የገበያ ሥርዓት ላይ ምርቶች ለገበያ መቅረባቸውን ጠቅሰው፤ ሌሎችንም ምርቶች በዚሁ ገበያ ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ ንግድ እንዲኖር ለማስቻል በግብርና ምርቶቻችን ላይ እሴት መጨመር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ለውጭ በሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ ከአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ጀምሮ እስከ ምርት ተቀባይ ደንበኛ ድረስ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ አሰራር ለመዘርጋት ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም