ኢትዮጵያ አፍሪካዊቷ አገር ሞዛምቢክ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነቷ ወቅት በጎ ሚና እንድትጫወት ጠየቀች

82

መስከረም 13 /2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ አፍሪካዊቷ አገር ሞዛምቢክ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አባልነቷ ወቅት በጎ ሚና እንድትጫወት ጥሪ አቀረበች።

77ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በድርጅቱ ዋና መቀመጫ ኒው ዮርክ ከመስከረም 3 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን ከተርኪዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶግሉ፣ከዩናይትድ ኪንግደም የልማት ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ እና ከሞዛምቢክ የውጭ ጉዳይና ትብብር ምክትል ሚኒስትር ማኑኤል ጎንካልቬስ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቶቹ የሁለትዮሽ ትብብርን ማጠናከርና የጋራ ፍላጎቶቻቸው በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

አቶ ደመቀ ከተርኪዬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ውይይት የሁለቱ አገራት ትስስር የወንድማማችነትና ፈተና ያልበገረው ግንኙነት መሆኑን አንስተዋል።

አገራቱ የትብብር መስኮቻቸውን በማሳደግ ይበልጥ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር አድርገዋል።

May be an image of 2 people, people sitting and indoor

አቶ ደመቀ ከዩናይትድ ኪንግደም የልማት ሚኒስትር ቪኪ ፎርድ ጋር ባደረጉት ውይይት በድርቅና በግጭት ለተጎዱ ወገኖች የሰብአዊ እርዳታ ማፋጠን እንደሚገባ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሞዛምቢክ የውጭ ጉዳይና ትብብር ምክትል ሚኒስትር ማኑኤል ጎንካልቬስ ጋር ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸው ወቅት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ ሞዛምፒክ እ.አ.አ በ2023 የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በምትሆንበት ወቅት በጎ ሚና ትጫወታለች ብላ እንደምትጠብቅ ገልጸዋል።

ማኑኤል ጎንካልቬስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አገራቸው በቅርቡ ላካሄደችው ምርጫ ላደረገችው ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነቷ “ለአፍሪካ ችግሮች የአፍሪካ መፍትሔ” መርህ እንደምትሰራ ገልጸዋል።ሞዛምቢክ እ.አ.አ ሰኔ ወር 2022 በተደረገ ምርጫ ከጃፓን፣ስዊዘርላንድ፣ኢኳዶርና ማልታ ጋር የምክር ቤቱ ተለዋጭ አባል ሆና ተመርጣለች።

እ.አ.አ ጥር 1 2023 አባልነቷን የምትረከብ ሲሆን ለሁለት ዓመት ቦታው ላይ ትቆያለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም