የመስቀል በዓልን ሃይማኖታዊ እሴቱንና የዓለም ቅርስነቱን በሚያጎላ መልኩ ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል

114

መስከረም 13/2015 (ኢዜአ) የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ እሴቱንና የዓለም ቅርስነቱን በሚያጎላ መልኩ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የመስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ ባሻገር ኢትዮጵያዊ  አንድነት  የሚንፀባረቅበት  መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዓሉ በዩኔስኮ በማይዳሰስ ቅርስ ተመዝግቦ ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘ በመሆኑ በርካታ ቱሪስቶች ይታደሙበታል፡፡

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደስታ ሎሬንሶ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዓሉ ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባለፈ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ መስህብነቱ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ነው።

ኃላፊው አክለውም የዘንድሮውን የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ እሴቱንና የዓለም ቅርስነቱን በሚያጎላ መልኩ በአዲስ አበባ ለማክበር ከተለያዩ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በተለይም በክብረ በዓሉ የኢትዮጵያን አስደናቂ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶች ዓለም እንዲገነዘብ የሚያደርጉ ስነስርዓቶች እንደሚካሄዱ ጠቁመዋል።

በበዓሉ ለመታደም የሚመጡ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎችን ለማስተናገድ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

ለበዓሉ በሰላም መከበርም ከወዲሁ የጸጥታ አካላትና የመዲናዋ ነዋሪዎች በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም