በመስቀል ደመራ እና ኢሬቻ በዓላት የሚታደሙ የውጭ ሀገር ዜጎችን የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስጎብኘት ታቅዷል-ቱሪዝም ሚኒስቴር

17

መስከረም 13 /2015 (ኢዜአ) በመስቀል፣ደመራ እና ኢሬቻ በዓላት ለሚታደሙ የውጭ ሀገር ዜጎችን በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማስጎብኘት መታቀዱን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

በዓላቱ በድምቀት መከበራቸው ተቀዛቅዞ የነበረውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ተጠቁሟል።

በቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪዝም ቢዝነስ ልማት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ቴዎድሮስ ገበያው ለኢዜአ እንዳሉት፤ የመስቀል፣ደመራና የኢሬቻ በዓላት በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸው የቱሪዝም ፍሰቱን አሻሽሎት ነበር።

ሆኖም በኮቪድ 19- ወረርሽኝ እንዲሁም በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ባሉ ግጭቶች ሳቢያ ላለፉት ጥቂት ዓመታት የውጭ ሀገራት ጎብኝዎች ቁጥር መቀነሱን ተናግረዋል።

ህዝባዊ በዓላት በሚከበሩበት ሰሞን የዓለም ቱሪዝም ቀንም ስለሚከበር አጋጣሚውን በመጠቀም የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ፍሰት እንዲጨምር ታቅዶ ወደ እንቅስቃሴ መገባቱን ጠቁመዋል።

በተለይም የበዓላቱን ልዩ መገለጫዎችና የዓለም ቅርስነትን በማስገንዘብም ብዙ ጎብኝዎች እንዲታደሙ በተለያዩ ስልቶች የማስተዋወቅ ስራ መጀመሩንም እንዲሁ።

የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ያሉት ባለሙያው፤ በዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት ምክረ ሀሳብ መሰረት የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማበረታታት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በዚህም በአሁኑ ወቅት የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥርና ፍላጎት ለማሳደግ መቻሉን አንስተዋል፡፡

ይህም ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ማደግ ብቻ ሳይሆን የውጭ ጎብኚዎችን በመሳብም ጭምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በመጪዎቹ ሳምንታት በሚከበሩት የመስቀል፣ደመራ እና የኢሬቻ በዓላትም በርካታ ጎብኝዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም