የኢትዮጵያና የግብፅ ግንኙነት እያደገ ነው- ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና የግብፅ ግንኙነት እያደገ ነው- ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ
አዲስ አበባ መስከረም 10/2011 የኢትዮጵያና የግብፅ ግንኙነት ፈጣን ዕድገት እያሳየ መምጣቱን ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ። ፕሬዝዳንቱ በኢትዮጵያ የግብፅ አምባሳደር የነበሩትን አምባሳደር አቡ ባክር ሄፍኒ መሃሙድን አሰናብተዋል። ከተሰናባቹ አምባሳደር ጋር ሁለቱ አገራት ስለነበራቸው ግንኙነት የተወያዩ ሲሆን ግንኙነቱ ጥሩ ዕድገት ያሳየና በተለይም ኢንቨስትመንቱ እንዲጠናከር አምባሳደሩ ያደረጉትን አስተዋፅኦ አድንቀዋል። አምባሳደሩ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የነበራቸው ቆይታ የተሳካ እንደነበር ጠቅሰው በቀጣይም ሁለቱ አገራት በኢንቨስትመንትና ተያያዥ የጋራ ጉዳዮች ላይ ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴም የሁለቱን አገራት ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም የበለጠ ማጠንከር የሚያስችላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል። ሁለቱ አገራት ያላቸውን ሁለንተናዊ ግንኙነት በቀጣይ በአዲስ መልክ የሚያስቀጥሉበትን ሁኔታም ፕሬዝዳንቱና አምባሳደሩ መምከራቸውን በፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት የፕሮቶኮልና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ለኢዜአ ተናግረዋል።