የኮሚሽኑ ሪፖርት አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለማዳን የተዘጋጀና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው

94

ሐዋሳ፤ መስከረም 13 / 2015 (ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት በአለም አቀፍ ጦር ወንጀል ሊጠየቅ የሚገባውን አሸባሪ ቡድን ለማዳን የተሰራና ፖለቲካዊ ወገንተኝነት የታየበት መሆኑን የደቡብ አመራር አካዳሚ አመራሮችና አሰልጣኞች ገለጹ፡፡

በኮሚሽኑ ሪፖርትና በአሸባሪው ህወሓት ሴራ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የደቡብ አመራር አካዳሚ ሃላፊዎችና አሰልጣኞች እንዳሉት ሪፖርቱ ለአንድ ወገን ያደላና ከመርህ ውጭ የአንድን ሉዓላዊት ሀገር ህልውና ክብር ዝቅ ለማድረግ የተዘጋጀ ነው ይላሉ፡፡

የአካዳሚው ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ሃላፊ አቶ አብዱልባር ኡስማን እንደገለጹት ኮሚሽኑ ያወጣው ሪፖርት "ተገቢውን የጥናት ሂደት ያልተከተለ ነው"፡፡

ሪፖርቱ በጦር ወንጀል ሊጠየቅ የሚገባውን አሸባሪ ቡድን ለማዳን የተሰራና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው በመሆኑ ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይችል ተናግረዋል፡፡

ሃያላን መንግስታት የህወሓትን ባህሪ ጠንቅቀው ያውቁታል ያሉት አቶ አብዱልባር በኮሚሽኑ በኩል የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለመጫን የሚጠቀሙበት ስልት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አገሪቱን ወደ ከፍታ በመመለስ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በማደናቀፍ ትልሟ እንዳይሳካ የተከፈተ ዘመቻ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ስትረጋጋ ጠንካራና የማትበገር ሀገር እንደምትሆን የሚያውቁ ሃያላን ሃገራትና ምዕራባዊያን ምቹ ሁኔታ እየጠበቁ ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚጠቀሙበት ስልት ነው ብለዋል፡፡

አገራቱ የአሸባሪውን ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር በመደገፍ ኢትዮጵያን ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማግለል የሚያደርጉት ጥረት ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት መንግስት በነበረበት ወቅት ህዝብና መንግስትን ለማሻገር የሚችል ራእይ እንዳልነበረው የሚናገሩት ደግሞ በአካዳሚው የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተርና የመሪነትና ኢንተርፕሪኒየርሽፕ አሰልጣኝ የሆኑት አቶ ዘነበ ዛፉ ናቸው፡፡

ቡድኑ የመንግስትነት ካባው ሲወሰድበት ከውሥጥም ከውጭም የኢትዮጰያ ታሪካዊ ጠላት ከሆኑ ሃገራትና ቡድኖች ጋር በማበር የሃገር ክህደት እየፈጸመ፣ተደጋጋሚ ጦርነት እየከፈተ ነው ብለዋል፡፡

አለም አቀፍ ተቋማት እያሳዳሩት ያለው ጫና ስጋት ብቻ ሳይሆን ይዞ የመጣው እድል መኖሩን የገለጹት አቶ ዘነበ በተባበሩት መንግስታት ጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያን አቋም የሚደግፉ ሃገራት መኖራቸውን እንደ ማሳያ በማንሳት ነው፡፡

እንደ አገር ጥንካሬያችንን ለማስቀጠል ውስጣዊ አንድነትን በማጠናከር የውጭ ጫናውን መቋቋም የሚያስችል አቅም መፍጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሃገር በመገንባት ሂደት ውስጥ እያንዳንዱ ዜጋ ድርሻው ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ዘነበ፤ በተለይ ምሁራን በውይይትና አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የዲፕሎማሲ ስራውን ማገዝ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ህወሓት ወደ እርቅ እንዲመጣ መንግስት ተደጋጋሚ የሰላም አማራጭ ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም ያሉት ደግሞ በአካዳሚው የስልጠና ቡድን አስተባባሪና በመሪነትና ሰው ሀብት አመራር አሰልጣኝ አቶ ጳውሎስ ባሳ ናቸው፡፡

የኮሚሽኑ ሪፖርትም ሆነ የምእራባዊያን መገናኛ ብዙሃን የሚያወጡት መረጃ አሸባሪው ቡድን የሚለቃቸውን ፕሮፖጋንዳዎች የሚያስተጋቡና ከእውነት የራቁ መሆናቸውን በማከል፡፡

የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ባዋቀራቸው የባለሙያዎች ቡድን አማካይነት ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደ ዜጋ የማይቀበሉትና ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩ ሃያላን ሀገራትን ለማስደሰት የተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ባለሙያዎቹ በሰጡት አስተያየት በቅኝ ያልተገዛችው ኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞዋን ለማረጋገጥ እየሄደች ያለችው ርቀት በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ያላትን አቅም የሚያሳድግ በመሆኑ በሃያላኑ ሃገራት አልተወደደላትም፡፡

በመሆኑም ጠንካራ መንግስትና ሀገር እንዳይኖር ህወሓት በውክልና የሚያደርገውን ጦርነት በአንድነት መመከት ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም