የሰብዓዊነት ካባ የደረበው ሴራ

144
  • ሪፖርቱ የመንግሥት የሠላም ጥረትን ታሳቢ ያላደረገ ነው፤
  • የመንግሥት ተባባሪነትን በማሳነስ ጫና ለመፍጠር ያለመ ነው፤
  • ቀደም ሲል የተደረገው ጥናት ለጣልቃ ገብነት አመቺ ባለመሆኑ የፈጠረው ስጋት፤
  • የሪፖርቱ ዓላማ እጅ በመጠምዘዝ ፖለቲካዊ ውሳኔ ለማሳለፍ ያለመ ነው። 

ለወትሮው ግጭት በማይለያት አፍሪካ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ጠንካራ መንግሥታት ለሠላምና መረጋጋት የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ አሳንሶ መመልከት አይቻልም። የኢትዮጵያ ሠላምና መረጋጋትም በብዙ መልኩ ከዚህ ውጭ ተነጥሎ የሚታይ አይሆንም። ኢትዮጵያ ለዓለም ታስፈልጋለች፤ ዓለምም ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል።

ይህ ሲሆን ግን በመከባበር እና ዓለም አቀፍ ሕግና መርህን የተከተለ ሊሆን ይገባዋል። ከዛ አለፍ ሲልም የዓለም ሥርዓት እና ፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ይጠበቃል።

አሁን ላይ እየሆነ ያለው ግን በዚህ መልኩ አይደለም። አገራት ለጋራ ጥቅማቸው እና ለዓለም ሠላም ሲሉ የተቀበሏቸው ዓለም አቀፋዊ ሕግጋት እና መርሆዎች ሲጣሱ ይታያል።

ለዓለም ሠላም እና ደህንነትን መጠበቅ፣ በሀገራት መካከል መልካም ግንኙነቶችን ለማዳበር እና ማህበራዊ ዕድገትን፣ የተሻለ የኑሮ ደረጃን እና የሰብዓዊ መብቶችን ለማስጠበቅ የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የቆመለትን ዓላማ የሚፃረር ድርጊት ሲፈጽም እየተስተዋለ ነው።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የሰየመው የሰብዓዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተቀሰቀሰው ጦርነት ‘ተከሰቱ’ ያላቸውን የመብት ጥሰቶች አስመልክቶ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርትም የሆነው ይኸው ነው። በዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) ኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመውን የፍርደ ገምድልነት ታሪክ ደግሞታል።

የአንደኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅን ተከትሎ ለዓለም ሠላምና ፍትህ የሚሰራ ዓለም አቀፍ ተቋም እንዲኖር በመሻት የተመሰረተው የመንግሥታቱ ድርጅት ኃያላን አገራት በአቅመ ደካማ አገራት ላይ የግፍ ወረራና ጥቃት ሲፈጽሙ አደብ ማስገዛት ሳይችል ቀርቷል።

እ.ኤ.አ በ1930’ዎቹ ጣሊያን የማኅበሩ መስራችና አባል በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ግልጽ ወረራ ስትፈጽም ከይስሙላ ማዕቀብ ባለፈ ታሪክ ይቅር የማይለው ፍርደ ገምድልነትን አሳይቷል። በእነዚህ እና በሌሎች መሰል ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶቹ ምክንያት ማኅበሩ ለቆመለት ዓላማ መጽናት ተስኖት ከአሳፋሪ ታሪኩ ጋር ረጅም ርቀት ሳይጓዝ ፍፃሜውን አግኝቷል።   

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መገባደድ በኋላም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የዓለም መንግሥታት ማኅበር የፈጸመውን ስህተት እንደማይደግም ታሳቢ ተደርጎ እ.ኤ.አ በ1945 በአሜሪካ ሳን ፍራንሲስኮ ጉባዔ እንዲመሰረት ሆኗል።  

በቻርተሩ መሰረት የድርጅቱ ዓላማዎች ዓለም አቀፍ ሠላምና ደህንነትን ማስጠበቅ፣ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ማድረግ፣ ሰብዓዊ ድጋፍን ማድረስ፣ ዘላቂ ልማትን ማስተዋወቅ እና ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያስከብር ሆኖ ሲቋቋም ዓለም ብዙ ተስፋ ጥሎበት ነበር።

ሆኖም ግን ተመድ ለአባል አገራቱ የሠላምና የፍትህ ፍላጎት ድምጽ ከመሆን ይልቅ ለአንዳንድ ኃያላን አገራት ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሆን ከጀመረ ውሎ አድሯል። የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አጣሪ የባለሙያዎች ኮሚሽን ኢትዮጵያን አስመልክቶ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው ሪፖርትም የዚሁ ማሳያ ነው።

በዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር መስፍን ጌታቸው ሪፖርቱ ቀደም ሲል በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ የተደረገውን ምርመራ የሚቃረን መሆኑን ነው የገለጹት።

ሪፖርቱ “ያልተሟላ እና ተያያዥነት የሌለው እንዲሁም በመረጃ ያልተደገፈ” ከመሆኑ ባለፈ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለማጠልሸት የታለመ ሴራ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለውታል።

ዶክተር መስፍን አክለውም ምዕራባውያን ቀደም ሲል የተደረገው ጥናት በኢትዮጵያ ጣልቃ ገብነት እንዲኖር ለተወጠነው ዕቅድ አልመች ሲላቸው እንዲህ ዓይነቱን የተዛባ ሪፖርት ወደ ማውጣት መሄዳቸውን ይናገራሉ።

ሪፖርቱ የመንግሥትን የሠላም ጥረት ታሳቢ አያደርግም ያሉት ተመራማሪው በሰብዓዊነት ካባ የተሸረበው ሴራ የመንግሥት ተባባሪነትን በማሳነስ ጫና መፍጠር ነው ይላሉ። ከዚህ ሻገር ሲልም የመንግሥትን እጅ በመጠምዘዝ ወደ ፖለቲካዊ ውሳኔ ለማስኬድ እንደሆነም ያስረዳሉ።

ኮሚሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙ ግድያዎች፣ አካላዊ ጥቃቶች፣ መድፈር እና ወሲባዊ ጥቃቶችን በመጥቀስ በሪፖርቱ ላይ ያቀረበ ሲሆን የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ተፈጽመዋል ባላቸው የመብት ጥሰቶች ላይ አጀንዳ አድርጎ እንዲመክርበት ጠይቋል። በዚህም ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ሲያወጣ በግልጽ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ሀሳቦችን አንጸባርቋል።

ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን በኢኮኖሚም ሆነ በተለያዩ መስኮች ለማንበርከክ እና አጣብቂኝ ውስጥ ለማስገባት የማይታክቱ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት በመንግሥታቱ ድርጅት በኩል ጫና ለመፍጠር ያለመ ፖለቲካዊ ሴራ ነው።

ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ሂደት እና የተሰጠው ኃላፊነት ግልፅነት የጎደለው ከመሆኑ ባሻገር ተገቢ ያልሆነ የፖለቲካ ቅኝት እንዳለው የሚያሳይ ነው። የኮሚሽኑ ሪፖርትም የተነሳበትን የፖለቲካዊ ፍላጎት ያንጸባረቀ እንጂ ትክክለኛ እና ተገቢ ጥናትን መሰረት ያደረገ አልነበረም።

ሪፖርቱ ቀደም ሲል የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽህፈት ቤት እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጥምረት ያደረጉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ እንዲሁም የጥምር ምርመራ ቡድኑ ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በተገቢው መልኩ ታሳቢ ያደረገ እንዳልሆነ በግልጽ አሳይቷል። ይህ ደግሞ ፍላጎቱ ፖለቲካዊ እንጂ የሰብዓዊነት ጉዳይ አለመሆኑን ተጨማሪ ማሳያ ማቅረብ አያሻም።

ምዕራባውያን በሰብዓዊነት ሽፋን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርጉት ጥረት አገራዊ ልዑላዊነትን የሚፃረር ከመሆኑ ባሻገር በየትኛውም መለኪያ ተቀባይነት እንደማይኖረው ግልጽ ነው።

አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ቤንጃሚን ኖርቶን የአገሪቱን ኮንግረስ የጥናት አገልግሎት መረጃን ዋቢ በማድረግ ባወጣው ጽሁፍ አሜሪካ እ.አ.አ ከ1991 ወዲህ 251 ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቶችን በአገራት ላይ በመፈጸም ጦርነቶች እንዲከሰቱ ምክንያት መሆኗን አስፈሯል። የበዙት የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት ደግሞ የጣልቃ ገብነቱ ሰለባ ናቸው።

የጋዜጠኛ ቤንጃሚን ሀሳብን በመጋራት አሜሪካ በአገራት የውስጥ ጉዳዮች ላይ የማያቋርጥ ጣልቃ ገብነቷን ዳግም ልታጤነው እንደሚገባም የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋን ዌንቢን በቅርቡ የማሳሰቢያ ሀሳብ ሰንዝረዋል።

ምዕራባውያን በቀጥታ ከሚያደርጉት ጣልቃ-ገብነት ሌላ እንደ ተመድ ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኩል የሚፈጥሩት ጫና እና ጣልቃ-ገብነትም የዚሁ ተቀጥላ እንደሆነ የሚታወቅ ነው።

አሁንም የኮሚሽኑ የተጠዳደፈ ሪፖርት በበቂ ማስረጃ ሳይደገፍ እና ሙያዊ ኃላፊነትን በተላበሰ አኳሃን አለመዘጋጀቱ ጫና ለመፍጠር ያለመ እና የስውር ጣልቃ ገብነቱ (Subtle Intervention) ነጸብራቅ ነው።

ኮሚሽኑ የመንግሥትን መሠረታዊ አቋም ባገናዘበ እንዲሁም የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሥርዓት የብሄራዊ የሕግ ሥርዓቱ ደጋፊ እና ሟሟያ በመሆን ኃላፊነቱን በሚገባ ሳይወጣ ቀርቷል። በዚህም የአሟይነት መርህ ባከበረ እና ተገቢነት ከሌላቸው የፖለቲካ ፍላጎቶች ነፃ በሆነ መንገድ ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ ይፋ ባደረገው ያልተሟላ ሪፖርት ራሱን አጋልጧል።

መነሻና መድረሻውም በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ጉባዔ ኢትዮጵያን አጀንዳ በማድረግ የአንዳድ አገራት ፖለቲካዊ ፍላጎት ለማስፈጸም ድብቅ ተልዕኮ እንዳለው የሚያሳይ ነው።

ይህን መሰሉ ፀረ-ኢትዮጵያ እንቅስቃሴ አገራዊ አንድነትን በማጠናከር እና ከመንግሥት ጎን በመቆም በሰብዓዊነት ካባ የተሸረበውን ሴራ ማክሸፍ ይገባል። ለዚህ ደግሞ መንግሥት ከሚያደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ባለፈ ዜጎች እና የኢትዮጵያ ወዳጆችን በማስተባበር ዕውነታውን ለዓለም ማኅበረሰብ ማሳወቅ ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም