አሸባሪው ህወሓት ለግል ጥቅሙ ሲል በአገር ላይ ውድመት ሲያስከትል የኖረ ለኢትዮጵያ የማይበጅ ነው -- የህግ ምሁራን

11

ሀዋሳ መስከረም 12/2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት ከምስረታው አንስቶ በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዘመናት የግል ፍላጎቱን ለማሳካት ሀገር የማፍረስ የጥፋት ስራሰራ የኖረና ለኢትዮጵያ የማይበጅ ቡድን ነው ሲሉ የህግ ምሁራን ገለጹ።

አሸባሪው ህወሃት ገና ከጥንስሱ ጀምሮ ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያን ህዝብ ለመበተን የወጠነውን ሴራ ከግብ ለማድረስ ስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ብዙ ግፎችን ፈጽሟል።

በራሱ ከሚፈጽማቸው እኩይ ተግባራት ባለፈ ጸረ ኢትዮጵያ ዓላማ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ሃይላትን ከውስጥም ሆነ ከውጭ በማደራጀት ግፎቹን ቀጥሎበታል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የህግ ምሁራን አሸባሪው ቡድን ለሀገርና ህዝብ የማይመጥን ሰብአዊነት የለሌውና ካለ ግጭት መኖር የማይችል መሆኑ ገልጸው በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚሽን ያወጣው ሪፖርት በህዝብ የተጠላን አሸባሪ ቡድን እንደገና ከሞት ለማንሳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው ይላሉ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሽመልስ አሻግሬ እንዳሉት አሸባሪው ቡድን ከቀደመ ታሪኩ አንስቶ የሚታወቀው በጦርነት ነው።

“ቡድኑ በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ ባሉት ጊዜያት በተደጋጋሚ በአማራና አፋር ክልሎች ያደረሰው ጉዳት በሀገሪቱ ላይ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ያሳደረባት ነው” ብለዋል።

በተለይም ቡድኑ ጦርነቱን የእርሻና ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት ላይ የሚያደርገው በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማሳደር አስቦ ያደረገው መሆኑን አክለዋል።

ከቀደመ ታሪኩ ብንነሳ ህወሃት ጦርነትን እንደ አንድ ትልቅ መፍትሄ የሚያይ ለመደራደር እንኳን የማይመችና ሰላም የማያወርድ መሆኑ እንደሚታወቅ ተናግረዋል።

“በህወሃት ውስጥ ጦርነትንና ሽብርን የሚቃወም አዲስ ትውልድ እስካልተፈጠረ ድረስ መሳሪያ ይዞ የሚንቀሳቀስ ድርጅት እንደመሆኑ ከአሸባሪው ድርጅት አዲስ ነገር ይወለዳል የሚል ዕምነት የለኝም” ሲሉም ተናግረዋል።

በደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ ከፍተኛ የህግ ባለሙያ አቶ ግርማ እርገጠው በቅርቡ ሾልኮ በወጣው የጥፋት ሰነዱ የደቡቡን የአገራችን  ህዝቦችን ለማታለል መንግስትን የሚቃወሙ የ"ፌደራሊስት ሃይሎች" ከሚላቸው ጋር በተጠናከረ መንገድ ግንኙነቱን በማደስ፣ የክልልነት ጥያቄን ለፖለቲካ ፍላጎቱ ለመጠቀም ማሰቡን እንደ ማሳያ ወስደዋል።

"ቡድኑን ከሞት ለማዳን አንዳንድ ምዕራባውያን እየተራወጡ ነው" ያሉት አቶ ግርማ በሰብዓዊ መብት ጥሰት ስም ሪፖርት በማዘጋጀት ለአሸባሪው የወገነ የሀሰት ትርክት ይዘው እንደመጡ ጠቁመዋል።

ከእውነታ ያፈነገጠው ሪፖርት አዘገጃጀት የህግ ክፍተት ጭምር ያለበት መሆኑን ጠቁመው ሆን ተብሎ መንግስትን ጫና ውስጥ ለመክተት የተዘጋጀ ፍርደ ገምድል ነው ብለዋል።

"ስልጣናችንን ለማስመለስ ገሀነም እንገባለን" ያለው ይህ አሸባሪ ቡድን ዛሬም በተደጋጋሚ እየጎዳ ያለው ህዝቡ እንደሆነና ህዝባዊ ባህሪ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል።

ህወሃት ህዝብን ከመጉዳት፣ ከመበዝበዝ ውጭ ምንም የማይጠቅም ቡድን ነው ያሉት አቶ ግርማ እንኳን ለሌላው ቀርቶ ለትግራይ ህዝብም እንማይፈይድ ተናግረዋል።

ሀገራችን ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎችን ለማክሸፍ እውነትን የያዝን እኛ ከመንግስት ጎን በመሆን በቻልነው ሁሉ በመረባረብ ሀገራችንን መጠበቅ ይገባናል ሲሉ ነው ምሁራኑ መልዕክት ያስተላለፉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም