የሴቶችን ሰቆቃ የካደው ሰነድ

101

በሰለሞን ተሰራ

በርካቶች አገርን በሁለንተናዊ ጽናቷ በሴትነት ይመስሏታል። በሆደ ሰፊነቷ በእናትም፤ በሚስትም ይወክሏታል። በአገራችን ተጨባጭ እውነታ ሴት ልጅ ጉልበቷ ሳይጠና፣ የልጅነት ቡረቃዋን ገታ አድርጋ ቤተሰቡን የመንከባከብ ከባድ ኅላፊነት ትሸከማለች።

ለዚህ ዕውነታ ክብር የማይሰጡ እሳቤዎች ግን አሉ። ለሴት እና አገር ክብርና ፍቅር ከመንፈግ አልፈው፤ ያጠቡ ጡቶቻቸውን፣ ያጎረሱ እጆቻቸውን የሚነክሱ ባለክፉ ምግባር ስብስቦች አሉ። የአሻባሪው የሕወሃት አስተሳስብና ተግባርም ለዚህ ሁነኛ አብነት ነው።

ይህ ቡድን አገር አይገደውም። የሴት ልጅ ክብርና ዋጋ አይገባውም። ይህ ቡደን ግና ከምስረታው ጀምሮ በሴትና በአገር ላይ በደልና ግፍን የባህሪ ገንዘቡ ያደገ ነው። ጫካ ውስጥ እያለም በጫካ አስተሳስብ በሴቶች፣ በህጻናነትና በመላ ንጹሃን ላይ ያልፈጸመው አሰቃቂ ግፍ የለም።

በስልጣን ዘመኑም ከወጣት እስከ አዛውንት፣ ከሕጻናት እስከ እናቶች ወጣቶችን የአፍ ጉቦ እያጎረሰ፣ በገቢር ግን በደምና ስጋቸው እየነገደ ኖሯል። በአገዛዝ ዘመኑም ከአገርኛ ባህልና እሴቶች ያፈነገጡ ነውሮችን ፈጽሟል። የአገርን ክብር የሚያዋርዱ፣ የሴቶችን ሕሊና የሚያደሙ፣ ትውልድ አምካኝ ዕኩይ ተግባራትን ሁሉ ፈጽሟል። ቡድኑ በሕዝብ እምቢተኝነት ከመንበረ ስልጣኑ ተግፍቶ ወደመቀሌ ከመሸገ በኋላም በሴቶችና አገር ላይ ግፍ ማድረሱን ቀጥሎበታል።

‘ጉድና ጅራት ከወደኋላ ነው’ እንዲሉ አበው የዚህ ቡድንም ትክክለኛ ቁመና ይፋ የሆነው በእብሪትና ጥላቻ ተመርቶ ወረራ ከፈጸመበት ቅጽበት ጀምሮ ነበር። በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ባደረገው የክህደት ጭፍጨፋ ከፈጸማቸው አሳፋሪ ታሪካዊ ግፎቹ አንዱ በሴቶች ላይ ያደረሰው ግፍ ነበር። ሴት የመከላከያ ሰራዊት አባላትንና የሰራዊት ቤተሰቦችን ጡት መቁረጥን ጨምሮ ለዕዝነ ልቦናና ለዐይነ ሕሊና የሚከብዱ ጭካኔዎችን አሳርፏል።

ወረራ በፈጸመበት ቅጽበት የሴት ልጅ ሀፍረተ ገላ ተደፍሯል። የእናትነት ክብሯ ተዋርዷል። አንገቷን እንድትደፋ፣ ቅስሟ እንዲሰበር ተደርጓል። ለመንገርም ሆነ ለመስማት የሚከብዱ፣ ትውልድ መቼም የሚያፍርባቸው ነውሮች ተፈጽሞባቸዋል።

የሴቶች መብትና ሰብዓዊ መብቶች ላይ ሰርክ የሚነዙ ሃሳዊ ምዕራባዊ የመብት ተማጓች ነን ባይ ቡድኖችና ልሂቃን ግን የዚህን ቡድን በሴት ልጆች ላይ የተፈጸሙ ነውሮችን ባልሰማ አልፈውታል። ምክንያቱም ይህ ቡድን ከጫካ ጀምሮ እነዚህ አካላት በአንቀልባ አዝለው ያሳደጉት ልጃቸው ነውና። በዚህም ቡድን መወገዙን ያወግዛሉ፤ አሸባሪውን የሚነካባቸውን ያሳድዳሉ። የአሸባሪው ህወሃትን በደም የጨቀየ ማንነት ማውሳት አይሹም። ይህም ትክክለኛ ማንነታቸው ሰብዓዊ መብት ሽፋን ዓላማቸውን ማሳካት እንጂ በሐቁ ግድ እንደማይሰጣችው ያረጋገጣል።

የቡድኑ ግፈኝነት አባዜ ከውልደቱ የመጣ ነው። “ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንዲሉ በእርጅና ዘመኑም “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ሆኖበት አመሉ አለቀቀውም። በመቃብር አፋፍ ተጎልቶ የልጅነት ዕኩይ እየፈጸመ ቀጥሏል። ለዚህም ከጫካ ጀምሮ የነበሩ የቡድኑ አባላት ዋቢ ናቸው።

የቀድሞ የህወሃት መስራች አመራር አቶ ገብረመድሀን አርዓያ በ1975 አካባቢ የሕወሃት ቡድን በራሱ አባላት ላይ የፈጸመውን ግፍ እንዲህ ይገልጻሉ። “በርሐ እያለሁ ከአዲስ አበባ ንግድ ትምህርት ቤት የተማረች የራያ ጨርጨር ልጅ ሚስት ነበረችኝ። የስምንት ወር እርጉዝ ሳለች አንድ ዕለት ስብሃት ነጋ መጣና ክሳድ ግመል ያለው ሬዲዮ ጣቢያችን በአይሮፕላን እንዳይመታ ሌላ ቦታ መውሰድ እንፈልጋለን እነ እገሌ ይሄዳሉና አብረህ ሂድ አለኝ፡፡ እንደማይመለከተኝ ገልጨ እምቢ ብልም ሰዎች አብረሃቸው እንድትሄድ ፈልገዋል በሚል ሸነገለኝ። ልክ እኔ እንደሄድኩ ለእርጉዝ ሚስቴ መድኃኒት ነው ብለው ከመጠን በላይ ክሎሮኪን ግተው ገደሉብኝ” በማለት በሴት ላይ ቡድኑ የፈጸመውን አሳዛኝ ታሪክ ያወሳሉ።

ይህ ቡድን የቀደመ ባህሪው በጥላቻ ተመስርቶ ዛሬም ወረራ በፈጸመባቸው አጎራባች አካባቢዎች ያልፈጸመው በደል የለም። የወራሪው የህወሃት ታጣቂዎች በአፋርና አማራ ክልሎች የፈጸሙት ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃቶች እንደማህበረሰብ ሰብዓዊ ክብር ለመግፈፍ፣ ለማዋረድ ሆን ብለው እንደፈጸሟቸውም ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ቢሮ ጥምር ጥናት ድምዳሜ ባሻግር ራሳቸውም በኩራት እየተናገሩ የፈጸሙት ነበር። ታጣቂዎቹ ሴቶችን ያለ ልዩነት በግፍ፣ በጭካኔ፣ በግልጽ የበቀል ስሜት ተነሳስተው በቡድን ደፍረዋል።

በደፈሯቸው እንስቶች ቤተሰብ ፊት የጠብመንጃ አፈ ሙዝን ጨምሮ ባዕድ ነገር በማህፀናቸው እየከተቱ የጭካኔ ጥግን አሳይተዋል። የሕወሃት አመራሮች በጫካ የለመዱትን ነውረኛ ባህላችው ለተተኪ ታጣቂዎች አውርሰው ዕኩይና አሳፋሪ ግብራቸውን ፈጽመዋል። ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃትን ስልታዊ የጦርነት ዓላማ   አድርገዋል።

አንዳንድ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ኃያላን አገራት ግን የዚህን ነውር ጌጡ የሆነን አሸባሪ ቡድን የከረፋ ገመና ለመሸፈን እየተጣደፉ ነው፡፡ ከሰሞኑ ይፋ ያደረጉት ስሁት የጥናት ሰነድም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ዕውነቱን በመሸሸግ፣ አሸባሪው ሕወሃትን ከመፈጸማቸው በደሎች ለማንጻት ብቻ ሳይሆን በተቃራኒው ‘የእምዬን ወደ አባዬ’ አድርጓል። መከላከያ ሰራዊቱ በዳይ፣ አሸባሪው ሕወሃት ተበዳይ ሆነው ቀርበዋል፤ በዚህ የሰብአዊ መብት ጥሰትን ሽፋን በማድረግ በተዘጋጀው የፖለቲካ ሰነድ።

የአሸባሪው ህወሃት ኃይሎች በአፋርና አማራ ክልሎች የሚገኙ ቦታዎችን ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ጊዜያት በተናጠል እና በቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በሕፃናት ሴቶችና አረጋዊያን ሴቶች ላይ መፈጸማቸውን በጣም በተድበሰበሰ መልኩ የሚጠቅሰው ሪፖርቱ እጀግ አስነዋሪ የሕወሃትን ገመናዎች ክዷል። ይህም የግፍ ሰለባ የሆኑ የአማራና አፋር ክልል ሴቶችን  ባልሻረ ቁስል ላይ እንጨት መስደድ ይመስላል።

የሕወሃት ጨካኝ ወራሪዎች ሰለባዎች መካከል በደቡብ ጎንደር ዞን ጋይንት ወረዳ ንፋስ መውጫ ከተማ አንዲት እናት በቡድን ተድፈራ ደም ይፈሳታል። ከጎረቤት ሲያስቷምሟት ሰንብትው በሳምንቱ ሌሎች የሽብር ቡድኑ አባላት በድጋሚ በቡድን ደፍረዋት የፌስቱላ በሽታ ተጠቂ ሆናለች።

ይቺ ምስኪን ሴት የተፈጸማባትን ግፍ “አንደኛው ታጣቂ ሊደፍረኝ ሱሪዬን ሲያወልቅ ደም ሲመለከት አስጠላሁት እና ተፋብኝ፤ ሰደበኝ እኔም ተስፋ ቆርጨ ራሴን ላጠፋ እያሰብኩ ስለነበር አልፈራሁትም፤ መልሼ ስሰድበው ተናዶ የጠመንጃውን አፈ ሙዝ በማህፀኔ ውስጥ ከተተው። ሕመሙ ከአቅም በላይ ስለነበር ራሴን ሳትኩ፡፡ አሁን ለፊስቱላ በሽታ ሕክምና እየተከታተልኩ ነው” በማለት ታስታውሳለች።

በዚሁ ከተማ የ30 አመቷ ወይዘሮ ገበያነሽ “ያደረጉብኝን ነገር መናገር ለእኔ ቀላል አይደለም፡፡ ሶስቱ ታጣቂዎች ልጆቼ እያለቀሱ ፊታቸው እየተፈራረቁ ደፍረውኛል፡፡ ትልቁ ልጄ 10 አመቱ ነው። ሌላኛው 9 አመት ሲሆን ሲደፍሩኝ እያዩ ያለቅሱ ነበር፡፡ ታጣቂዎቹ የሚፈልጉትን ካደረጉ በኋላ ትተውኝ ሄዱ፡፡ የቻሉትን ከዘረፉ በኋላ ፀያፍ ስድብ አወረዱብኝ መሳሪያቸውን ደቅነው እንደሚገድሉኝ አስፈራሩኝ“ ሲሉ ገልጸው ነበር።

በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት የሕወሃት ወራሪዎች በአማራ ክልል ሴቶችን በዘረኛ እና አጸያፊ ስድብ ታጅቦ በርካታ ሴቶችን ደፍረዋል። በሪፖርቱም በንፋስ መውጫ ብቻ 16 ሴቶች ላይ በመሳሪያ አስፈራርተው አስገድደው መድፈር የተፈጸመባቸው ሲሆን ከነዚህም መካከል 14ቱ በቡድን የተደፈሩ ናቸው። በሌላ በኩል በ10 ቀናት ብቻ በዚሁ አካባቢ ከ70 በላይ ሴቶች ላይ አስገድዶ የመድፈር ወንጀል በሽብር ቡድን ተፈጽሟል።

በሰሜን ጎንደር ደባርቅ ወረዳ ድብባህር ቀበሌ ነዋሪ የሆነች ሴት ከነሐሴ 14 ቀን እስከ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ባሉት 15 ተከታታይ ቀናት በተለያዩ 15 የትግራይ ወራሪ ኃይሎች ተደፍራለች። “እኔ ቤቴ እያለሁ ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. 2 ታጣቂዎች መጥተው አንዱ ደፈረኝ። እስከ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በየተራ እየመጡ ይደፍሩኝ ነበር።15 ታጣቂዎች እየተመላለሱ ደፍረውኛል” በማለት ሐቁን አስረድታለች።

በአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ ዞን ያሎ ወረዳ ነዋሪ የሆነች ተጎጂ አንድ ታጣቂ ቤቷ መጥቶ የባሏን መሳሪያ እንድትሰጠው ሲጠይቃት ባለቤቷ ምንም አይነት መሳሪያ እንደሌለው በመግለጿ ካራ አውጥቶ ሊወጋት ሲል ይተወኛል በሚል ብር እንደሰጠችውና ብሩን ከወሰደ በኋላ ግን በልጆቿ ፊት አስገድዶ እንደደፈራት ማስረዳቷም ተገልጿል።

በአምነስቲ ሪፖርት መሰረት “ከጉዳቱ ሰለባዎች የሰማናቸው ማስረጃዎች የህወሃት ታጣቂዎች የፈጸሙት ተግባር የጦር ወንጀል እን በሰብዓዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ተግባራቸው የሰውን ልጅ ክብር ያጎደፈ እና ሰብዓዊነትን የሚጻረር ነው” በማለት ነበር የገለጸው። የዚህ ወንጀል ድርጊት ያስፈጸሙ አመራሮችና ወንጀል ፈጻሚዎቹን ለፍርድ ማቅረብ እንዳለባቸውም የድርጅቱ ዋና ፀሃፊ አሳስበው ነበር።

ዳሩ ‘ጽድቁ ቀርቶ በቅጡ በኮነነኝ’ ሆና ነገሩ የአሻበሪው ቡድን አባላትን ለሕግ እንዲቀርቡ ካመድረግ ይልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘመቻቸው በተቃራኒነ ሆኗል። አሸባሩው ቡድፍን በከፈተኛ ውሶስተኛ ዙር ወረራ ተመሳሳይ ግፎች እና ጾታዊ ጥቃቶችን አባብሷል። አዲስ የምርመራ ግኝት ባሉት ስሁት ሰነድ የህወሃትን የግፍ ካባ አውልቆ፣ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ እንዲሉ ጥፋቶችን ወደሌላ አካል ለማላከክ ይሞክራል።

ኢትዮጵያን ከኋላ ሆነው ሲጋልቧት የኖሩ ኃያላን አሁን ላይ በእምቢ ባይ ትውልዱ ተጋድሎ እጃችሁን ከጫንቃዬ ላይ አንሱ ሲባሉ የፈረሳቸውን ልጓም በማጥበቅና ጋሻ ጃግሬዎቻቸውን በማሰለፍ አገሪቱን ዳግም እንቅልፍ ሊነሷት እየተወራጩ ነው፡፡

የዚህ አካል የሆነውና በሰብዓዊ መብት ሽፋን ብቅ ያለው ሪፖርት ከላይ ከተዘረዙት በላይ የከፋውን የህወሃትን ግፍና በደል በመሸፋፈን መንግስትን ተጠያቂ ለማድረግ እየተንደፋደፉ ነው። ኢትዮጵያውያን አሸባሪው ህወሃት ፈረስ መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ። በእናት የምትመሰለው ኢትዮጵያና ልጆቿ የተደፈሩት በሽብር ቡድኑ ብቻ ሳይሆን በጋላቢዎቹም ጭምር መሆኑን ይረዳሉ፤ እውነታውም እርሱ ነው።

በርግጥም በኢትዮጵያና ልጆቿ ላይ እየተፈጸመ ያለው ደባ አሸባሪው ህወሃትና ጋላቢዎቹ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የሚሄዱበት አካሄድ አካል ነው። በጥናት ሽፋን ያዘጋጁት የፖለቲካ ሰነዳቸውም ለትግራይ ህዝብ በመጨነቅ ሳይሆን ሞልቶ የፈሰሰሰውን የግፍ ጸዋቸውን ለመሸፋፈንና ኢትዮጵያን የመበታተን አካሄዳቸው እንዲሰምርላቸው በመሻት ነው።  

ይህንን የተረዳ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የአሸባሪው ህወሃት የግፍ ጥግና የአንዳንድ ምእራባውያንን ሴራ በሚገባ በመረዳት አገርን ለማዳን በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት እንደየ ሙያው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት አቅሙ በሚፈቅደው መጠን ሊያበረክት ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም