ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ምርመራ መርህን ከሚያከብሩ ተቋማት ጋር በትብብር መስራቷን ትቀጥላለች--አምባሳደር ዘነበ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ምርመራ መርህን ከሚያከብሩ ተቋማት ጋር በትብብር መስራቷን ትቀጥላለች--አምባሳደር ዘነበ
መስከረም 13/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ምርመራ መርህን ከሚያከብሩ ተቋማት ጋር በትብብር መስራቷን እንደምትቀጥል በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ ተናገሩ።
የአሸባሪው ህወሃትን የፖለቲካ መግለጫ የሰብዓዊ ምርምራ ሪፖርት አስመስሎ ለማቅረብ የሚደረግ ጥረትን ኢትዮጵያ በፅኑ የምታወግዘውና የማትቀበለው መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ አካሂጄዋለሁ ያለውን የሰብዓዊ መብት ምርምራ ሪፖርት ላይ ትናንት ውይይት ተደርጓል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ሪፖርቱ ከደረጃ በታች የሆነ፣ ሙያዊ ይዘት የጎደለውና ግድ የለሽነት የተሞላበት በመሆኑ እንደማይቀበለው አስታውቀዋል።
አምባሳደር ዘነበ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የምርመራ ተቋማት ጋር መርኸን በጠበቀ መልኩ ስትሰራ መቆየቷን ጠቅሰዋል።
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሰብዊ መብት ጥሰቶች ላይ ምርመራ እንዲያደርጉ አስፈላጊውን ሁሉ ትብብር ማድረጓን በመጥቀስ።
ሆኖም በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ታህሳስ 2014 ዓ.ም ላይ በጄኔቫ ሌላ ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው የባለሙያዎች ኮሚሽን ለማቋቋም የውሳኔ ሀሳብ ሲቀርብ ኢትዮጵያ መቃወሟን ገልጸዋል።
የተቃውሞው መነሻ ደግሞ ሀገር ላይ ጫና በማሳረፍ ፖለቲካዊ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚፈልጉ ኃይሎች ያዘጋጁት እቅድ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ባለሙያዎች ስራ ሲጀምሩ ኢትዮጵያ አሁንም አቋሟን በማጽናት ፖለቲካዊ ተልዕኮን ለማሳካት ከሚንቀሳቀሱ ባለሙያዎች ጋር እንደማትሰራ መግለጿንም ገልጸዋል።
ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም በጥምር መርማሪ ቡድኖች የተካሄደውን ምርምራ ዋጋ ዝቅ የሚያደርግ ተግባር መፈጸማቸውንም አመላክተዋል።
ለዚህም ማሳያው የወጣው ሪፖርት ለአንድ ወገን ያደላና በህወሃት የሽብር ቡድን የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ያልዳሰሰ፣ የሰብዓዊ መብት ምርምራ መርሆን ያላሟላና ፍርደ ገምድልነት የታየበት ነው ብለዋል።
በመሆኑም የአሸባሪው ህወሃትን የፖለቲካ መግለጫ የሰብዓዊ ምርምራ ሪፖርት አስመስሎ የማቅረብ እርምጃን ኢትዮጵያ በፅኑ የምታወግዘውና የማትቀበለው መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በጥምር መርማሪ ቡድን የወጡ ምክር ሀሳቦችን ለመተግበር መንግስት የሚኒስትሮች ግብረኃይል አቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩን ዓለም ሊገነዘበው እንደሚገባ ገልጸዋል።
በቀጣይ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች መርኸን ከሚያከብሩ ተቋማት ጋር መስራታችንን እንቀጥላለ ሲሉም አስረድተዋል።