ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ሱዳን የወዳጅነት የእግር ኳስ ጨዋታቸውን ዛሬ ያካሂዳሉ

መስከረም 13 /2015(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን(ዋልያዎቹ) ከሱዳን አቻው ጋር ከሚያደርጋቸው ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች መካከል የመጀመሪያውን ዛሬ ያካሄዳል።

ጨዋታው ከረፋዱ 4 ሰአት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይከናወናል።

የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለጨዋታው መስከረም 9 ቀን 2015 ዓ.ም ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል።

የድሬዳዋ ከተማው ግብ ጠባቂ ዳንኤል ተሾመ በሕመም ምክንያት ቡድኑን እንዳልተቀላቀለ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ላለፉት ሁለት ቀናት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዱን አድርጓል።

በመጀመሪያው ቀን ልምምድ ላይ ያልነበረው የአጥቂ መስመር ተጫዋቹ ዳዋ ሁቴሳ ቡድኑን በመቀላቀል ልምምዱን አድርጓል።

በግብጽ ኤል-ጉና ክለብ የሚጫወተው የመሐል ክፍል ተጫዋች ሽመልስ በቀለ በቡድኑ ስብስብ ከተካተቱ ተጫዋቾች መካከል ይገኝበታል።

ብሔራዊ ቡድን ከሱዳን ጋር ሁለተኛ የወዳጅነት ጨዋታውን መስከረም 16 ቀን 2015 ዓ.ም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ያደርጋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስፖርቱ ቤተሰቡ ጨዋታዎቹን በነጻ በመታደም ብሔራዊ ቡድኑን እንዲያበረታታ ጥሪውን አቅርቧል።

በፊፋ ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ ኢትዮጵያ 138ኛ፤ ሱዳን ደግሞ 130ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም