ክልሉን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው- ቢሮው

70

ሐዋሳ፤ መስከረም 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) የሲዳማ ክልልን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

በባለፈው የበጀት ዓመት ክልሉን ከጎበኙ ቱሪስቶች 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጀጎ አገኘው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና የጸጥታ ችግር ምክንያት የቱሪዝም እንቅስቃሴው ተቀዛቅዞ ቆይቷል።

ዘርፉን ከተጋረጠበት ተግዳሮት ለማላቀቅና ክልሉን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።የሲዳማ ክልል በቱሪዝም ሀብት የበለጸገ መሆኑን አመልክተው፤ ''በባህላዊ፣ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ የተጎናጸፍናቸውን ጸጋዎች በማልማት የቱሪስት ፍሰቱን ለማሳለጥ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው'' ብለዋል።

በዚህ ረገድ የሐዋሳ ኃይቅን ከማስዋብ ባለፈ ገራምባ ተራራ እና ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ የማህበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም ልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።

የክልሉ መንግሥት በመደበው 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ወጪ ግንባታው እየተካሄደ ያለው የገራምባ ተራራ ማህበረሰብ አቀፍ የቱሪዝም ልማት ፕሮጀክቶች የመጀመሪያው ምዕራፍ ሥራ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

የልማት ሥራው ከኢትዮጵያ ደንና ዱር ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የ500 ሜትር መወጣጫ ደረጃ መጠናቀቁን ተናግረዋል።

ጥብቅ ደኑን ከማህበረሰቡ በመረከብ የሕግ ማእቀፍ ወጥቶለት፣ በጽህፈት ቤት፣ በሥራ አስኪያጅና በስካውት ጥበቃ የማደራጀቱ ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስረድተዋል።

ቢሮው የውጭ ሀገር ቱሪስትን ለመሳብ በክልሉ ያሉ የመስህብ ስፍራዎችንና የቱሪስት መዳረሻዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጽና በሌሎችም አማራጮች እያስተዋወቀ እንደሚገኝ አመላክተዋል።በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት ሀብቶች አካባቢ ሰላም ለማረጋገጥ ህዝብን መሰረት ያደረገ የጸጥታ ስራ በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ማሪማ በበኩላቸው በክልሉ ያሉ ተፈጥሮአዊ ፣ባህላዊና ታሪካዊ ቦታዎችን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በክልሉ ልዩ የቱሪዝም መርሃ ግብሮችን ሳይጨምር ዘጠኝ የቱሪስት መዳረሻዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ በኢትዮጵያ ብቻ ከሚገኙ 25 ብርቅዬ አዕዋፍት መካከል 16ቱ በክልሉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

የቱሪስት ፍሰቱን ለማነቃቃትና የመስህብ ስፍራዎች ለማስተዋወቅ እንዲቻል ቱሪዝሙን ዲጅታል የማድረግ ሥራ እንደሚከናወን ተናግረዋል። የሲዳማ ክልል አዲስ የቱሪዝም 'ብራንድ' በዚህ ዓመት ይፋ ይሆናል ብለዋል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን በወረዳዎችና ከተሞች ለማስፋፋት ትኩረት መሰጠቱን አብራርተዋል።

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የሚያስችል ጉዞ በማካሄድ የውጭ ባለሀብቶችን በዘርፉ ለማሳተፍ ጥረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

ባለፉት 12 ወራት ክልሉን ከጎበኙ ቱሪስቶች 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም አመልክተው፤ ገቢው የተገኘው በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት መስህቦችን ከጎበኙ ከ3 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ጐብኝዎች ነው ብለዋል።

ሕይወታቸውን በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ያደረጉ ማህበራት፣ ምግብ አብሳዮች፣ አስጎብኝዎች፣ የባህል ምሽት ቤቶች፣ የእደ ጥበብ ማህበራት፣ሆቴሎች፣ ሎጆች እና ሌሎችም አገልግሎት የሚሰጡ አካላት ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን “አዲስ እሳቤ ለቱሪዝም” በሚል መሪ ቃል በክልሉ ከመስከረም 26 እስከ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም