በሰሜን ጎንደር ዞን በአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎቹ የተደፈረሩ ሴቶች ለማይጠገን የስነ-ልቦና ችግር መጋለጣቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ጎንደር ዞን በአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎቹ የተደፈረሩ ሴቶች ለማይጠገን የስነ-ልቦና ችግር መጋለጣቸውን ገለጹ

መስከረም 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በሰሜን ጎንደር ዞን በወረራ በቆየበት ወቅት በታጣቂዎቹ የአስገድዶ መደፈር ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች ለማይጠገን የስነ-ልቦና ችግር መጋለጣቸውን ገለጹ።
የቡድኑ ታጣቂዎች የጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶች ለጤናና ለስነ-ልቦና ችግር ተጋላጭ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአሸባሪው ቡድን አባላት ሴቶችን በቡድን በመድፈር የከፋ ሰብዓዊ ጉዳት ከማድረሳቸውም በላይ ከኢትዮጵያውያን እምነት፣ ባህልና ወግ ውጭ የሆነ ድርጊት መፈማቸውን የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴቶች ገልጸዋል።
በቤተሰብ ፊት አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በእድሜ የገፉ እናቶችንና ህጻናትን ጭምር መድፈራቸውን አመልክተዋል።
የቡድኑ ታጣቂዎች ጸያፍ ድርጊት ሰለባ የሆኑ የሰባት ልጆች እናትና የ57 ዓመት እድሜ እናት የደረሰባቸው ጥቃት በማህበረሰቡ ውስጥ ቀና እንዳይሉ ያደረጋቸው መሆኑን ተናግረው፤ በህይወት ከመቆየት ሞትን እንደሚመርጡ ገልጸዋል።
ታጣቂዎቹ ጥቃት እንዳይፈጽሙባቸው ቢማጸኗቸውም ሊሰሟቸው እንዳልፈቀዱ ገልጸው፤ በስለት የአካል ጉዳት እንዳደረሱባቸውም ጠቅሰዋል።
የአሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች ተፈራርቀው የደፈሯቸው በመሆኑ በወቅቱ ራሳቸውን ስተው እንደነበር አስታውሰው፤ አሁንም የጤናቸው ሁኔታ አስከፊ እንደሆነ ተናግረዋል።
በባህር ዳር ከተማ ሕክምና ቢያገኙም አሁንም ከፍተኛ የሕመም ስሜት እንዳላቸው ገልፀዋል።
ከጤና ቀውሱ በላይ የአካባቢውን ማህበረሰብ ለማየት የሚችሉበት አቅም በማጣታቸው ወደቀዬአቸው መመለስ እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።
ሁለት ልጆቻቸው ቡድኑን ለመፋለም የጸጥታ አካላትን ተቀላቅለው ወደ ግንባር መዝመታቸውን ገልጸዋል።
ሌላዋ የቡድኑ ጥቃት ሰለባ የ25 ዓመት ወጣት በበኩሏ በአካባቢው የነበረ አንድ የአጎቷን ልጅ በጥይት አቁስለው ወደቤት ገብተው በቡድን እየተፈራረቁ እንደደፈሯት ገልጻለች።
ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስባት በመስጋት ሁለት ሕጻናትን በመያዝ ለሦስት ሳምንት በጫካ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ማሳለፏን አስረድታለች።
ጥቃቱ ከደረሰባት በኋላ በወቅቱ ህክምና ሳታገኝ በመቅረቷ ለጤና ችግር መጋለጧን ተናግራለች።
የህወሓት የሽብር ቡድን የጥፋት ሃይል በመሆኑ ሁሉም ሊከላከለው እንደሚገባ ገልጻለች።
የአማራ ሴቶች ማህበር የሰሜን ጎንደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሰብለ ባየህ በበኩላቸው አሸባሪ ቡድኑ ታጣቂዎች ከፈጸሙት ዘርፋና ውድመት ባለፈ ንፁሃንን መግደላቸውን፣ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውንና አስገድደው መድፈራቸውን ተናግረዋል።
የቡድኑ ታጣቂዎች በዓለም አቀፍ ህግ የሚያስጠይቅ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መፈፀማቸው አስረድተው፤ በዞኑ በርካታ ሴቶች መደፈራቸውን አመልክተዋል።
እስካሁን ድረስ ጥቃት የተፈፀመባቸው 67 ሴቶች ብቻ ችግራቸውን በድፍረት በማሳወቅ ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።
የጥቃቱ ሰላባ የሆኑት በርካቶቹ የህብረሰቡን ተፅኖ በመፍራት እራሳቸውን እንደደበቁ ተናግረዋል።
ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች የህክምናና ሌሎች ድጋፎች እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁንም ሰፊ ድጋፍ እንደሚፈልጉ አመልክተዋል።