የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቻው ጋር ያደረገው ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቻው ጋር ያደረገው ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቀቀ
መስከረም 12 /2015 (ኢዜአ)በአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣርያ አንደኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አቻው ጋር ያደረገ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
አህጉራዊው ውድድር በሰኔ ወር 2015 ዓ.ም በሞሮኮ አስተናጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ አገራትን ለመለየት የሚካሄደው ማጣሪያ በያዝነው ሳምንት መጀመሩ ይታወቃል።
በማጣሪያው ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዛሬ በአበበ በቂላ ስታዲየም ከዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባደረገው የማጣሪያ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይቷል።
ብሔራዊ ቡድኑ የመልስ ጨዋታውን መስከረም 27 ቀን 2015 ዓ.ም በኪንሻሳ ያደርጋል።
ቡድኑ በደርሶ መልስ ውጤት ተጋጣሚውን ካሸነፈ በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም ከአልጄሪያ አቻው ጋር በሁለተኛው ዙር ጨዋታውን ያደርጋል።
በሶስት ዙር የሚካሄደው የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ የማጣሪያ ውድድር ከአስተናጓጆ ሞሮኮ ውጪ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ሰባት የአፍሪካ አገራትን ለመለየት የሚካሄድ ነው።
በፓሪስ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የእግር ኳስ ውድድር ከስድስት አህጉራት ኮንፌዴሬሽኖች የተወጣጡ 16 አገራት ይሳተፋሉ።