የአሶሳ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን የዘይት ፋብሪካ ምርቱን ወደ 10ሺህ ሊትር ለማሳደግ እየሰራ ነው

34

አሶሳ መስከረም 12 / 2015 (ኢዜአ)  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የሚገኘው የአሶሳ ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን በ89 ሚሊዮን ብር የማስፋፊያ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ፡፡

እየተካሄደ ባለው የማስፋፊያ ስራ ምርቱን በቀን ወደ 10ሺህ ሊትር በማሳደግ ስራ እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካውን በዚህ አመት በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ ለማስገባት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ምክክር ተካሂዷል፡፡

የዩኒየኑ ስራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ቸኮል በአሁኑ ወቅት የፋብሪካው የማስፋፊያ ህንጻ ግንባታ መጠናቀቁን ጠቁመው በዚህ ዓመት መጨረሻ የማሽን ተከላ እና ሌሎች ስራዎች ተጠናቀው በሙሉ አቅሙ ማምረት እንደሚጀምር ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

የማስፋፊያ ግንባታው መጠናቀቅ ፋብሪካው አሁን ያለውን በቀን 1ሺህ 500 ሊትር የማምረት አቅም ወደ 10 ሺህ ሊትር እንደሚያሳድገው ስራ አስኪያጁ አመላክተዋል፡፡

ፋብሪካው ከዩኒየኑ አባላት እና ከአርሶ አደሮች ጥሬ ዕቃ በመሰብሰብ አሁን በግብዓትነት ከሚጠቀመው የኑግ ሰብል በተጨማሪ ሌሎች የቅባት ሰብሎችን በመጠቀም ስራ እንደሚጀምር አስታውቀዋል፡፡

"የፋብሪካው ማስፋፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ 150 ለሚጠጉ ሰዎች የስራ ዕድል ይፈጥራል" ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ግብርናና ገጠር ልማትና የተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮዎች እንዲሁም የክልሉ እና የፌደራል ህብረት ስራ ማስፋፊያ ተቋማት አመራሮች ለአርሶ አደሮች ዩኒየን መጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም