የሽብር ቡድኑ በደቡብ ወሎ ከ128 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ላይ ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል-አስተዳደሩ - ኢዜአ አማርኛ
የሽብር ቡድኑ በደቡብ ወሎ ከ128 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ላይ ዘረፋና ውድመት ፈጽሟል-አስተዳደሩ
ደሴ፤ መስከረም 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን በወረራ በቆየበት ጊዜ ከ128 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ላይ ዘረፋና ውድመት ቢፈጽምም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጠያቂ አለመደረጉ መላውን ህዝብ አሳዝኗል ሲል የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን ለኢዜአ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት በዞኑ በወረራ በቆየበት ወቅት ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል፡፡
"ንጹሃንን በግፍ ጨፍጭፏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ የሚችለውን ንብረት ዘርፏል፣ ያልቻለውን ደግሞ ዳግም አገልግሎት እንዳይሰጥ በማድረግ አውድሟል" ብለዋል፡፡
ቡድኑ በመንግስትና በህዝብ መገልገያ ተቋማትና ንብረቶች ላይ ያደረሰው ዝርፊያና ውድመት 104 ቢሊዮን ብር ግምት እንዳለውና ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ደግሞ የግለሰቦች ንብረት ላይ የተፈጸመ መሆኑን አብራርተዋል።
ቡድኑ በዞኑ 242 የጤና፣ 230 የትምህርት፣ 87 የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ 109 ኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ተቋማትን ሙሉ በሙሉ ማውደሙን የክልሉ መንግስትና የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ በጋራ ባስጠኑት ጥናት መረጋገጡን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
"ደሴና ኮምበልቻ በክልሉ ከፍተኛ የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመትን ከተሞች በመሆናቸው በአማራ ክልል ከደረሰው አጠቃላይ ውድመት 45 በመቶ በደቡብ ወሎ የደረሰ መሆኑን በጥናቱ ተረጋግጧል" ብለዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ለመግለጽ የሚዘገንንና አስነዋሪ ግፍና በደል በህዝብ ላይ ቢፈጽምም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጠያቂ አለመደረጉ መላው የኢትዮጰያ ህዝብን ያሳዘነና ያስቆጣ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
አሁንም የዓለም ህዝብና ተቋማት በሃሰተኛ መረጃ ከመንጠልጠል ይልቅ መሬት ላይ ያለውን ትክክለኛና ሐቅ ተገንዝበው የሽብር ቡድኑን በዓለም አቀፍ ህግ ተጠያቂ በማድረግ ፍትህን ሊያሰፍኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ቡድኑ የአርሶ አደሩን የእርሻ በሬ ጭምር አርዶ ከመብላት ባለፈ በጥይት ጨፍጭፎ በእንሰሳት ላይም ግፍ የፈጸመ አረመኔ መሆኑን ጠቁመው የህብረተሰቡን ቀለብ ሽሮና በርበሬ ሳይቀር የዘረፈ ነውረኛ ቡድን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አሸባሪ ቡድኑ በዞኑ ከ2ሺህ 600 የሚበልጡ መኖሪያ ቤቶች ላይም በከባድ መሳሪያ ጭምር ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ 617 ቤቶችን ከእነ ሙሉ ንብረታቸው ማውደሙንም አመልክተዋል፡፡
"ቡድኑ ይህን ሁሉ ግፍ ሲፈጽም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዳላየ ከማለፍ ባለፈ "ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮሃል" እንደሚባለው ችግሮችን ተቋቁሞ ለትግራይ ህዝብ እርዳታ የላከውን መንግስት ለመክሰስ የሚደረግ ጥረት ተቀባይነት የለውም" ሲሉ አስገንዝበዋል።
"ቡድኑ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያደርገውን መፍጨርጨር የኢትዮጵያ ህዝብ አንድነቱን ጠብቆ መመከትና ዳግም ውደመት እንዳያደርስ መረባረብ ይኖርበታል" ሲሉ አመልክተዋል ፡፡
በዞኑ በተሁለደሬ ወረዳ የቀበሌ 07 ነዋሪ አርሶ አደር ይማም መሃመድ በበኩላቸው የሽብር ቡድኑ ያልፈጸመባችው ግፍና መከራ አለመኖሩን ሀዘንና ቁጭት በተቀላቀለበት ስሜት ገልጸዋል፡፡
"በቤቴ ውስጥ የነበረን ንብረት በሙሉ በመዝረፍ፣ ያስቀመጥኩትን 92 ሺህ ብር በመቀማትና በመጨረሻም ቤቴን በማቃጠል ግፍና መከራ ፈጽሞብኛል" ሲሉ በቡድኑ የተፈጸመባቸውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ገልጸዋል ፡፡
"ለእነርሱ ይብላኝላቸው እንጅ የተቃጠለው ቤቴም መልሶ እየተሰራ ነው፣ ንብረቱንም እተካዋለሁ" ብለዋል።
አርሶ አደር ይማም አክለው "ቡድኑ ዳግም የከፈተብንን ጦርነት በጋራ ለመመከት ዝግጁ ነን፣ ስንቅም እያዘጋጀን ነው" ሲሉ አሁን ላይ ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት የከፈተውን አሸባሪ ቡድን እየተፋለመ ላለው መከላከያ ሰራዊት ከህብረተሰቡ ጋር ሆነው እየተወጡ ስላለው የደጀንነት ሚና ተናግረዋል ።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሀገር የማፍረስ ሴራውን ለማሳካት ከሚጠቀምባቸው እኩይ ተግባራት አንዱ በአምራች ኢንዱስትሪዎችና በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ውድመት በማድረስ መንግስትና ህዝብ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጫና በመፍጠር ስለመሆኑ በቅርቡ ባዘጋጀው የጥፋት ሰነድ ማረጋገጡ ይታወቃል።