የተመድ የሰብአዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ከደረጃ በታች የሆነ፣ሙያዊ ይዘት የጎደለውና ግድ የለሽነት የተሞላበት ነው-አምባሳደር ዘነበ ከበደ

24

መስከረም 12 /2015 (ኢዜአ) “ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች የባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ከደረጃ በታች የሆነ፣ሙያዊ ይዘት የጎደለውና ግድ የለሽነት የተሞላበት ነው” በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ ገለጹ።

የኮሚሽኑ ሪፖርት በሰብአዊ መብት ሽፋን ስም ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን የማስፈጸም ተልዕኮ ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።

51ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን ከመስከረም 2 ቀን 2015 ዓ.ም በስዊዘርላንድ ጄኔቫ እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል።

ምክር ቤቱ ዛሬ በ11ኛ ቀን ውሎው በኢትዮጵያ ላይ አሳታፊ ውይይት(Interactive Dialogue) እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በአገሪቷ ያለውን የሰብአዊ መብት ሁኔታ እንዲያጣራ የተቋቋመው የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት አዳምጧል።

በጄኔቫ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዘነበ ከበደ ሪፖርቱን አስመልክቶ በጽሁፍ የተዘጋጀ ምላሽ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ በተመድ የሰብአዊ ምክር ቤት ኢ-ፍትሐዊና ፖለቲካዊ አላማ ያለው ጫና ሲደረግባት እንደቆየ አምባሳደር ዘነበ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ላይ እየደተደረገ ያለው ሐሰተኛ ዘመቻ ሊቆም ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረጉትን የጋራ ምርመራ መሰረት ያደረጉ እርምጃዎችን እየወሰደች እንደምትገኝ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብት ሕጎች ላሉባት ግዴታዎች ተገዢ ናት ሲሉ ነው የገለጹት አምባሳደሩ።መንግስት በሐሰተኛ መረጃዎች በምክር ቤቱ የተቋቋመውን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች የባለሙያዎች ኮሚሽን እንደማትቀበለው መግለጿን አስታውሰው ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት በወቅቱ ተቃውሞ ማሰማታቸውን አመልክተዋል።

ነገር ግን መንግስት ከኮሚሽኑ ጋር ሊሰራበት የሚችልባቸውን አማራጮች በማፈላለግና በማወያያት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።ኮሚሽኑ የተሰጠው ኃላፊነት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን የሰብአዊ መብት ሁኔታ እንዲያጣራ ቢሆንም ከተግባሩ ውጪ መላው ኢትዮጵያን በሪፖርት ውስጥ እሸፍናለሁ ማለቱን አመልክተዋል።

የኮሚሽኑ ሪፖርት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ያደረጉትን የጋራ ምርመራ የደገመና የተለየ ግኝት የሌለው እንደሆነ ነው አምባሳደር ዘነበ ያስረዱት።

ሪፖርቱ ሙያዊ ይዘት የሌለው፣ግድ የለሽነት የተሞላበት፣ከደረጃ በታች የሆነ፣አሳሳችና የፖለቲካ ተልዕኮ ያለው መሆኑንና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የተጠቀመባቸው መስፈርቶች ሳይንሳዊ ያልሆኑ ናቸው ብለዋል።

ሳይንሳዊ ጥናትን ከእማኞች መረጃን በስልክና በበይነ መረብ አማራጮች በሰበሰበው መረጃ ድምዳሜ ላይ መድረሱ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ነው ብለዋል።

ኮሚሽኑ አሸባሪው ሕወሓት በአማራና ክልል የፈጸማቸውን ወንጀሎች ማጣራት ሲገባው ወደ ጎን ማለቱ የሚያሳዝን ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል ዳግም ጦርነት መክፈቱንና ለሰብአዊ እርዳታ የተዘጋጀ ነዳጅ ላይ ዝርፊያ መፈጸሙን ነው አምባሳደሩ ያብራሩት።

ኮሚሽኑ አሸባሪው ሕወሓት ሕጻናትና ወጣቶችን በግዳጅ በመመልመል ለጦርነት ሲያሰልፍ ዝምታን መርጧል ብለዋል።

አምባሳደር ዘነበ ስለሆነም የተመድ የሰብአዊ ምክር ቤት አባላት ሪፖርቱንና የኮሚሽኑን የኃላፊነት ጊዜ ለማራዘም የሚደረጉ ሙከራዎችን ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

51ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ እስከ መስከረም 27 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም