ቀጥታ፡

በመጪው ቅዳሜ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚካሄድ ሰልፍ የለም

ደብረ ብርሀን መስከረም 10/2011 በደብር ብርሃን ከተማ በመጪው ቅዳሜ ሰልፍ እንደሚካሄድ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ ሀሰት መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ጸጥታና ሚሊሻ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መኳንንት አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው ቅዳሜ መስከረም 12/2011 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ ተፈቅዷል በሚል በማህበራዊ ሚዲያ እየተናፈሰ ያለው ወሬ ከእውነት የራቀ ነው። ከከተማው ህብረተሰብ የተውጣጡ ኮሚቴዎች በተጠቀሰው ዕለት በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ጥያቄ ቢያቀርቡም ካለው ሃገራዊ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ እንዳልተፈቀደላቸው አስታውቀዋል። "የሰልፍ ጥያቄው ዲሞክራሲያዊ አግባብ ያለው ቢሆንም በጸጥታ ኃይል ድጋፍና ጥበቃ ለማድረግ በቂ የዝግጅት ጊዜ ማድረግ ያስፈልጋል " ያሉት ኃላፊው ሰልፉ የሚካሄድበትን ጊዜ ወደፊት ከአስተባባሪ ኮሚቴዎች ጋር በመነጋገር ይፋ እንደሚደረግ አመልክተዋል። በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰልፍ ምክንያት ሁከቶችና ብጥብጦች ተቀስቅሰው በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይከሰት ጊዜ ተወስዶ በብስለት ለመምራት በቂ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ ህብረተሰቡም ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በመገንዘብ ሰልፉ እስኪፈቀድ በትግስት እንዲጠብቅ ኃላፊው ጠይቀዋል ። "ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቱ የተጀመረውን ለውጥ በማይደግፉ ጸረ- ሰላም ግለሰቦች አሉባልታ ሳይመራ የአካባቢውን ሰላም በንቃት ሊጠብቅ ይገባል " ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ። በሌላ በኩል ሰሞኑን በከተማው አንዳንድ አካባቢዎች ዝርፊያና ስርቆት እየተበራከተ በመሆኑ ቤት የሚያከራዩ ግለሰቦች የተከራዮችን ማንነት፣ የስራ ሁኔታና ውሎ በማወቅ አስጊ ጉዳዮች ሲያጋጥም ለፀጥታ አካላት እንዲያሳውቁም አሳስበዋል ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም