ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ነፃነትና ሉዓላዊነት አስከብሮ ለማስቀጠል በሁሉም መስክ መነሳት አለባቸው-ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ነፃነትና ሉዓላዊነት አስከብሮ ለማስቀጠል በሁሉም መስክ መነሳት አለባቸው-ምሁራን
መስከረም 12/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ነፃነትና ሉዓላዊነት አስከብሮ ለማስቀጠልና የውጭ ኃይሎችን ጫና ለመቋቋም በሁሉም መስክ በቁጭት መነሳት እንዳለባቸው ምሁራን ገለጹ፡፡
አሸባሪው ህወሓት ሀገር የማስተዳደር ዕድል አግኝቶ በነበረበት የአገዛዝ ዘመኑ የአንዳንድ ምዕራባውያንን ፖሊሲ በማስፈጸም ኢትዮጵያን ለድህነትና ኋላቀርነት ዳርጓታል፡፡
"ህብረ ብሔራዊ የፌደራሊዝም ስርዓትን" በስህተት የፖለቲካ መንገድ በመተግበር ዜጎችን በቋንቋና በዘር ከፋፍሎ ግጭቶችን በመቀስቀስ ሀገራዊ አንድነት እንዲዳከም ሰርቷል።፡፡
በሀገር ላይ ብዙ የጥፋት ሴራዎችን የሸረበው ይህ ቡድን፤ በህዝብ ቁጣ ከስልጣን ከተወገደ በኋላ የመከላከያ ሰራዊቱን ከኋላ በመውጋት የሀገር ክህደት ወንጀል ፈጽሟል።
ንጹሃንን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደልና ሀብትና ንብረታቸውን በመዝረፍ የዓለም አቀፍ ህግጋትን የጣሱ የሰውን ልጅ ሞራል የሚጻረሩ የሽብር ተግባራት ላይ ተሰማርቷል።
የሕግ ባለሙያው አቶ አብነት ዘርፉ ለኢዜአ እንዳሉት፤ አንዳንድ ምዕራባውያን የህወሓትን የሽብር ስራ አይተው እንዳላዩ በማለፍ በእያንዳንዱ እንቅስቀሴ በኢትዮጵያ ላይ ጣታቸውን ይቀስራሉ፡፡
የሽብር ቡድኑ ህፃናትን ለጦርነት ሲመለምል፤ ሰብዓዊ ድጋፍን ለጦርነት ዓላማ ሲያውል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ እያለፈው መሆኑን በመተቸት።
አሸባሪው ህወሓት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለሰብዓዊ ድጋፍ ማጓጓዣ ያስቀመጠውን 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ ሲዘርፍ ለይስሙላ ዝርፊያው ተገቢ አለመሆኑን ከመግልጻቸው ውጪ ዘራፊውን በሕግ ተጠያቂ አለማድረጋቸውም ሌላ ዓላማ እንዳላቸው ያሳያል ነው ያሉት።
ከዚህም ባለፈ የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈጸመበት ወቅት በጭና፣ ጋሊኮማ፣ ማይካድራና ሌሎች አካባቢዎች ንጹሃንን በጅምላ ሲረሽን ለምን ብሎ የጠየቀ እንደሌለ ጠቅሰዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ያቋቋመው የባለሙያዎች ኮሚሽን ከሰሞኑ ያወጣው ሪፖርት ህወሓት የፈጸማቸውን ግፎች በጨረፍታ ማለፉ የሽብር ቡድኑ የፖለቲካ ዓላማቸው አስፈጻሚ መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችና አንዳንድ ምዕራባውያን ከዓለም አቀፍ ሕግጋት በተጻራሪነት በመቆም አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን እንዲያዳክም ከጀርባው እየደገፉት እንደሆነ በመጠቆም።
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አቡሌ መሀሪ፤ የሽብር ቡድኑ የመኸር እርሻ ወቅትን ጠብቆ የከፈተው ጦርነት ሀገርን በኢኮኖሚ የማዳከም ድብቅ አጀንዳ ሊኖረው እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡
በአማራና አፋር ክልሎች ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ብቻ ባለፈው የመኸር ወቅት ከሶስት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ምርት ሳይሰበሰብ መቅረቱን በመጠቆም፡፡
በዝናብ በተመሰረተ ግብርና ላይ የተንጠለጠለው አርሶ አደር ለችግር ስለሚጋለጥ በመንግስት ላይ ያለውን ጫና እንዲበረታ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ይህንንም አንዳንድ ምዕራባውያን በሰብዓዊ ዕርዳታ ሰበብ ፖሊሲያቸውንና ስትራቴጂያቸውን ለማስፈጸም እንደ እጅ መጠምዘዣ ሊጠቀሙበት እንደሚሞክሩ ነው የተናገሩት፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ አብነት ዘርፉ አንዳንድ ምዕራባውያን ዓለም አቀፍ ስርዓቱን ሆነ ብለው የግል ፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ መንገድ እያደረጉት ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን የአንዳንድ ምዕራባውያን አድሏዊ አሰራር ገፈት ቀማሽ የሆንነው "ደሃ በመሆናችን ነው" የሚል ቁጭት አድሮበት ድህነትን ለማጥፋት መዝመት አለበት ብለዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያን ነፃነትና ሉዓላዊነት ማስከበርና የውጭ ጫናዎችን መቋቋም እንደሚቻል በመጠቆም።