በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ሶማሊያ ተግባራዊ የሚደረግ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ሶማሊያ ተግባራዊ የሚደረግ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
መስከረም 12 ቀን 2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ሶማሊያ ተግባራዊ የሚደረግ የከርሰ ምድር የውሃ ልማት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
ፕሮጀክቱ የምስራቅ አፍሪካ የከርሰ ምድር የውሃ ልማት ሲሆን በዓለም ባንክ በተገኘ ድጋፍ ገቢራዊ የሚደረግ መሆኑም ታውቋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ሀብታሙ ኢተፋ፣ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድን እንዲሁም የዓለም ባንክ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ሶማ ጎሆሽ ሞውሊክ በአዲስ አበባ ይፋ በተደረገው መርሃ ግብር ላይ ተገኝተዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፤ ፕሮጀክቱ የምስራቅ አፍሪካን የከርሰ ምድር ውሃ በአግባቡ በማልማት ለቀጣናው ዘላቂ ልማትና የውሃ አጠቃቀም እንደሚያግዝ ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ በሚተገበርባቸው ወረዳዎች ለአነስተኛ መስኖና የመጠጥ ውሃን ከማሻሻል ባሻገር ለቀጣናው መረጃ ልውውጥና ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ስራ አመራርን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ገልፀዋል።
ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ በሁሉም ወረዳዎች በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ እየተፈተኑ ላሉ ቆላማ አካባቢዎች ሁነኛ አማራጭ ስለመሆኑ አንስተው በኢትዮጵያ ከ8 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ከከርሰ ምድር ውሃ እንደሚጠቀምም አውስተዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትሯ አይሻ መሀመድ፤ የከርሰ ምድር ውሃ 60 በመቶውን የኢትዮጵያ ውሃ አቅርቦት ቢሸፍንም በአግባቡ አልተጠቀንምበትም ብለዋል።
ፕሮጀክቱ የከርሰ ምድር ውሃ ዘላቂነት ባለው መልኩ ለመምራትና ለመጠበቅ እንደሚያግዝ ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የቤት እንስሳት በድርቅ መሞታቸውን ገልፀው፤ በ55 ወረዳዎች ላይ የሚተገበረው ይህ ፕሮጀክት በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ውሃ በማጣት ለስደትና ችግር የሚጋለጡ ወገኖችን ለመታደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የ210 ሚሊየን ዶላር በጀት የተያዘለት የውሃ ልማት ፕሮጀክቱ ለሰዎችና የእንስሳት ውሃ መሰረተ ልማት በመዘርጋት ቀጠናዊ ትስስር ለማጎልበት እንዲሁም ለአገራዊ ዕቅዶችና ዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።
በድርቅ ተጎጂ አካባቢዎች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ገልፀው፤ የወቅቱ የከርሰ ምድር ውሃ አጠቃቀም በቅጡ ለመምራትና ለመጠቀም ለማህበራዊና የኢኮኖሚ ዕድገት ያግዛልም ነው የተባለው።
በዓለም ባንክ ለምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ሶማ ጎሆሽ፤ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ፣ ኬኒያና ሶማሊያ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ለመጀመሪያው የፕሮጀክት ክንውን ኢትዮጵያ 210 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዳገኘች ገልፀዋል።
ከነዚህ አገራት ቀጥሎም ደቡብ ሱዳንና ጅቡቲ የከርሰ ምድር ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት እንደሚተገበር ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ የገፀ ምድር ውሃ ቢኖራትም ስርጭቱ ወጥነት የሌለውና ለጎርፍ እንደሚዳረግ ገልፀው፣ ተቋማዊ ስራዎቾን በማጠናከር የከርሰ ምድር ውሃን ማልማት ወሳኝ ነው ብለዋል።
በፕሮጀክት በ55 ወረዳዎች ላይ የውሃ ፕሮጀክቶች በመገንባት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የድርቅ ተጋላጭ ወገኖች በመስኖ አገልግሎቶን በማስፋፋት ተጠቃሚ ያደርጋል፤መፈናቀልንም ያስቀራል ነው ያሉት።
ግብርና ምርታማነትን ማሳደግ በተለይም ለቁም እንስሳት ሀብት ልማትና የሰው ሀብት ልማት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ነው የተባለው።
በሌላ በኩል ለከርሰ ምድር ውሃ ጥናትና ስራ አመራር የሚያጠና ተቋማዊ አቅም ለመንገባት፣ ከቀጠናው አገራት ትስስርና ትብብር ለማጠናከር ያስችላል ነው ያሉት ፡፡