ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ሂደትን እንደሚደግፉ መግለጻቸው አሸባሪው ህወሓት ጦርነቱን ከመጀመሩ አንስቶ መንግሥት የያዘው አቋም ነው - አምባሳደር ስለሺ በቀለ

658

መስከረም 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) “ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ሂደትን እንደሚደግፉ የገለጹት ዐሳብ መንግሥት አሸባሪው ህወሓት ጦርነቱን ከመጀመሩ አንስቶ ሲያንጸባርቀው የነበረ ፍላጎት ነው” ሲሉ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ገለጹ።

77ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በድርጅቱ ዋና መቀመጫ ኒው ዮርክ በመካሄድ ላይ ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ትናንት በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር በኢትዮጵያ ያለው ግጭት መፍትሔ እንዲያገኝ አገራቸው የአፍሪካ ሕብረትን የሰላም ሂደት ትደግፋለች ብለዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ የፕሬዝዳንቱ ንግግር አሸባሪው ሕወሓት ጦርነቱን ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ መንግስት ከያዘው አቋም ጋር የተጣጣመ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።

መንግስት የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ጥረት እንዲሳካ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ጊዜ መግለጹ ይታወቃል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ-መንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በቅርቡ የሕብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዑክ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የኃላፊነት ጊዜ ማራዘማቸው የሚታወስ ነው።

የናይጄሪያ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የቀጠናው ልዑክ ሆነው የተሾሙት በነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም