ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተመድ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተመድ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ
መስከረም 12 ቀን 2015 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርአቶ ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
አቶ ደመቀ በትናንትናው ዕለት በተመድ የአካባቢ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን ጋር በኒውዮርክ ተወያይተዋል።
ውይይታቸው ኢትዮጵያ እያካሄደችው ባለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር እና በታዳሽ ኃይል ልማት ዙሪያ ያተኮረ ነበር።
በውይይቱ አቶ ደመቀ አትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና ለአረንጓዴ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራች መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ረገድ እየተተገበረ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግር ተጠቃሽ መሆኑን ያነሱት አቶ ደመቀ መርሃግብሩ ከሃገሪቱ ባሻገር ፋይዳው ለአጎራባች ሃገራት ጭምር መሆኑን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ እምቅ የታደሽ ኃይል ሃብቶቿን በማልማት ምጣኔሃብታዊ እና ማህበራዊ እድገትን ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች በማከናወን ላይ እንደምትገኝ በውይይቱ ተነስቷል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከታዳሽ የልማት ኘሮጀክቶች አንዱ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ደመቀ፤ ኘሮጀክቱ ከኢትዮጵያ ባሻገር ሌሎች የተፋሰሱ አገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በግድቡ ግንባታ ዙሪያ ያለውን አለመግባባት በንግግር ብቻ የሚፈታ እንደሆነ በማስረዳት ኢትዮጵያ ሁሌም ለንግግር እና ውይይት ዝግጁ መሆኗን አስረድተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ኢንገር አንደርሰን ኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማትን እውን ለማድረግ እየከናወነች ያለውን ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ታዳሽ ኃይል ልማትን ለማስፋፋት የኢትዮጵያ መንግስት የሚያደርገውን ጥረት የመንግስታቱ ድርጅት የአካባቢ ኘሮግራም እንደሚደግፍ የገለፁ ሲሆን የህዳሴ ግድብ አለመግባባት በውይይት የሚቋጭበት ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው 77ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እየተሳተፉ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ ጋርም ውይይት አድርገዋል።
ኮሚሽኑ በድርቅ እና ግጭት በአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ለመርዳት እያከናወናቸው ላሉ ተግባራት ምስጋና አቅርበው ፤ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፓ ግራንዴ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በቅርበት መስራቱን እንደሚቀጥል ተናግረዋል።