የሪፖርቱ ስውር አላማ ...

52

የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ምክረ ሃሳብ ኤስ-31/1 የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ቡድን የተቋቋመው ባለፈው ዓመት ወርሃ ህዳር ነበር። ኬኒያዊቷ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ በሰብሳቢነት ስቴቨን ራትነር የተባለ አሜሪካዊ እና ራዲካ ኮማራስዋኒ ሲሪላክዊት በአባልነት በማካተት ላለፈው አንድ ዓመት የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ሲሰራ ቆይቷል። ነገር ግን የምርመራ ቡድኑ የተቋቋመለት ስውር ዓላማ መኖሩን የተወሰኑ ነጥቦችን ከጥናቱ ግኝት በማጣቀስ መመልከት ይቻላል።

የሪፖርቱ አዘገጃጀት ኮሚቴ አባላት ስብጥር የራሱ መልክ ያለው ይመስላል። የጥናቱ ቡድን ሰብሳቢ ካሪቬቲ የጎረቤት ኬኒያዊት መደረጓና ሌላውም አባል ሲሪላንካዊ መደረጉ፣ አጥኚዎች ኡጋንዳ ውስጥ መሽገው ጥናት ያሉትን ስውር ተልዕኮ ያነገበ ስሁት ሪፖርት ያቀረቡበት መንገድ 'የአፍሪካን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል' የሚለውን እሳቤ የማይወዱ አካላት ጠንሳሽነት የአፍሪካን አገራት በአፍሪካዊያን ልሂቃን ችግር ውስጥ መክተት የሚለውን 'የእሾህን በእሾህ' ስልት የተከተለ ይመስላል።

ቡድኑ ከተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጽህፈት ቤትና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች የጋራ የምርመራ ሪፖርት ላይ ድክመት አለ ብሎ ካመነ ጥናቱን አሻሽሎ ማቅረብ ሲኖርበት እንደ አዲስ መጀመሩም በርግጥም ሌላ ዓላማ እንዳለው ያሳብቃል።

የጥናት ሪፖርቱ ከአጠናን ሳይንሳዊ ስነ ዘዴዎችና የትንታኔ ክሽፈቶች ባሻገር አገር ያወቃቸውን፤ ፀሐይ የሞቃቸውን እውነታዎች መካዱ አሳዛኝ ነው። ለአብነትም በአማራና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ ጥሰቶችን እንዳላየ ማለፉ ወይም አሳንሶ መመልከት ተስተውሎበታል።

ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመሆን የጋራ የምርመራ ሪፖርት ያወጣው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጽህፈት ቤትና በጥናቱ የተሳተፉ አካላት ለዚህ ጥናት ትብብር አላደረጉልኝም ብሎ በግልጽ ያስቀመጠ በመሆኑ  እንዴት አድርጎ ተአማኒ ጥናት ሊያጠና ይችላል የሚል ጥያቄ ይፈጥራል።

ይህ ቡድን ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ተንቀሳቅሶ መረጃ ሰብስቦ ሳይሆን ጥቂት ግለሰቦችን ኡጋንዳ ሆኖ በበይነ መረብ አነጋገርኩ በማለትና ተጨባጭነት በሌላቸው አሉባልታዎች ላይ በመመስረት ነው።

አሸባሪው ህወሃት ሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰውን ግፍ ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ጦርነት በማለት መግለጹ የአንድን ነገር ስረ መሰረት ማጣራት ያልቻለ ጥናት ተአማኒ ሊሆን አይችልም ያስብላል። በሌላ አገላለዕ የጥናቱ ቡድን አባላት አሸባሪ ቡድኑ ጦርነት መጀመሩን አያምኑበትም፤ ወይም ለመደበቅ ፈልገዋል ማለት ነው።

በሰነዱ ውስጥ ጅምላ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ዘር ማጥፋት የሚሉ ቃላትን ቢጠቀምም ለእነዚህ ቃላት ማስረጃው ግን የስልክ ልውውጥ መሆኑ አስገራሚ  ያደርገዋል። መቀሌ ለተደፈሩ ሴቶች ማስረጃው የህወሃት አባል የሆነን ሰው መጠየቅ ይመስላል ጥናቱ።

ይህ ቡድን በግብዓት እጥረትና መሰል ምክንያቶች የተጣለበትን ጥልቅ ምርመራ ማካሄድ እንደማይችል ቢያሳውቅም ዓላማው  በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳደር ያለመ በመሆኑ የጥናት መንገዶችን ሳያሟላም ድምዳሜ ላይ የደረሰ ይመስላል።

የጥናት ቡድኑ ከአዲስ አበባ ወጥቶ ወንጀሉ ወደተፈጸመባቸው ቦታዎች መሄድ እንዳልቻለ፣ የሱዳንና የጅቡቲ መንግስታትም በየአገራቱ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለማናገር ፈቃደኝነታቸውን እንዳልገለጹ ያትታል። ‘ከአዲስ አበባ አልወጣሁም፣ የጉዳት ተጠቂዎችን ማናገር አልቻልኩም‘ ቢልም እነማንና የት እንዳገኛቸው የማይታወቁ ሰዎች ደግሞ በደፈናው በጥናቱ ተጠቅሶ ይገኛል።

ቡድኑ በአካባቢው ሳይንቀሳቀስ ደደቢት ውስጥ ተፈናቅለው ትምህርት ቤት ውስጥ የተጠለሉ ዜጎች በድሮን ጥቃት እንደተገደሉ፣ ቦምቡም የቱርክ ድርጅት የሚያመርተው ቦምብ መሆኑን አረጋግጫለሁ ይላል። በስፍራውም ንጹሃን እንጅ ታጣቂዎች አብረው አልነበሩም ሲል በስፍራው የተገኘ መስሎ ይደመድማል።

አባሪው የሕወሃት ቡድን በበርካታ የአፋርና አማራ አካባቢዎች የፈጸማችውን ጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች እንደሁም ከጦርነቱ መጀመሪያ ዕለት አንስቶ የፈጸማችውን የጦር ወንጀል ስር የሚያጠቃልሉ ግፎችን አላካተም። ይህም የጥናቱ ጎዶሎነትን ያሳብቃል። ይልቁኑም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ባልዋለባቸው ጉዳዮች ለመኮንንና ለመወንጀል ስፍራዎችና ድርጊቶችን ዘርዝሯል።

ከጥናቱ ድምዳሜዎች መካከልም በመቀሌና አካባቢው ስፋት ያላቸው ጾታዊ ጥቃቶች በመከላከያ ሰራዊት እንደተፈጸሙ ቢያትትም መረጃውን ከየትና ከነማን እንዳገኘው አይገልጽም። ያገኘው መረጃው እውነት ስለመሆኑ ያቀረባቸው የሐቅ ማረጋገጫ መንገዶችን አላቀረበም።

በሌለ በኩል መከላከያ ሰራዊት በመቀሌ የተለያዩ ተቋማት ዘርፏል በሚል በጥቅሉ ቢወነጅልም የወንጀሉን ስፋት፣ መቼ፣ እንዴት የሚለውን ተጠየቅ የሚያብራሩ መረጃዎች ማቅረብ አልቻለም።

በሌላ በኩል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ውድመቶች በአማራና አፋር ክልሎችም በስፋት የተፈጸሙ ቢሆንም ይህ የጥናት ቡድን ግን ማካተት አልፈለገም። ለማስመሰል ሲባል የጭና እና የቆቦ ጅምላ ጭፍጨፋዎችን ቢያካትትም ከደረሰው ግፍና ዘር ማጥፋት ወንጀል አኳያ በደምሳሳው አልፎታል። አሸባሪውን ቡድን ወንጀሎች ለመሸፋፈን በገሃድ ወገንተኝነቱን አሳይቷል።

ይህ ጥናት ግኝት የትግራይ ታጣቂዎች በአማራ ክልል ቆቦና ጭና ንጹሃን መገደላቸውን፣ በተወሰነ መልኩ አስገድዶ መድፈርና ዘረፋ መፈጸማቸውን በጥቂቱ ቢገልጽም ይህን ያደረጉት ግን በትግራይ ሴቶች ላይ ለተፈጸሙ ጥቃቶች አጸፋና በቀል ሲሉ እንደሆነ ለመግለጽ ይዳዳዋል፤ የሴቶችን መከራ በቁጥር በማወዳደር በህዝብ ላይ ቀልዷል።

የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ አንድ ነገር ማድረግ አለበት የሚለው የጥናት ቡድኑ ጥሪ ከጀርባው የባዕዳን ተልዕኮ ስለመኖሩ መገለጫ ነው። ጥናቱ ተፈጸሙ ስለተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎች በዝርዝርና በስፋት ማጥናት ሲገባው ምክር ቤቱ ፖለቲካዊ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት የወገንኝነት ጥሪ አስተላልፏለ።

የኢትዮጵያ መንግስት ቀደም ብሎ በዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥምር የምርመራ ሪፖርት ጥቁምታዎች መሰረት ማድረግ ያለበትን ስራዎች ከጀመረ ሰነባብቷል። ይህ ሰሞነኛ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ቡድን የምርመራ ሰነድ ግን ዓለም አቀፍ ሕጐችን ከመጣሱ ባሻገር የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን ለማስፈን ያደረገውን ፈቃደኝነትና የወሰደውን እርምጃ እውቅና የነሳ ነው።

ኢጋድ፣ አፍሪካ ሕብረት እና የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡና በዓለም አቀፍ ህጎች ተጠያቂነት እንዲሰፍን በመወትወት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመድፈር ያለመ ሪፖርት ነው።

ሪፖርቱ መሬት ላይ ያሉ እውነቶችን የካደ ነው፤ በቅድመ ጦርነት የተደረጉ ጉዳዮችን የጠቃቀሰው ይህ ሰነድ፤ የኢትዮጵያ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ አደረጃጀቶች ለሰላም ያደረጉትን ጥረት አላወሳም። ጦርነቱ ከጀመረ በኋላም በየጊዜው መንግስት ለሰላም ሲባል የወሰዳቸውን የሰላም አማራጮችን አላነሳም።

የትግራይ ሴቶች የኢትዮጵያና የኤርትራ ሃይሎች እንዲሁም በፋኖ ሃይሎች ሰብዓዊ ክብንራቸውን በሚያወርዱ ስድቦች እየተሰደቡ ተደፍረዋል የሚለው ይህ ሪፖርት በአማራና አፋር ክልሎች የአሸባሪው የሕወሃት ቡድ ከህጻናት እስከ መነኩሴዎች ለሰሚ ጆሮ በሚሰቀጥጥ ሁኔታ የቡድን አስገድዶ መድፈሮችን በየስፍራው መፈጸማቸው የአደባባይ ሐቅ ቢሆንም ይህ ዕውነታ ተክዷል።

በሌላ በኩል በአፋር ክልል ከፍተኛ ጥፋት ያደረሰው አሸባሪው ህወሓት የ263 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ዳሩ ግን ይህ የምርመራ ሪፖረት እነዚህን እውነታዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማድረስ አልፈለገም። አሸባሪው ቡድን ከንጹሃን ጭፍጨፋ ባሻገርም በሰው ልጆች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችና የጦር ወንጀሎችን ማንሳል አልፈለገም።

አሸባሪው ቡድኑ ወረራ በፈጸመባቸው የአማራና አፋር ክልሎች ሁለንታናዊ ውድመቶችን ብቻ ሳይሆን በትግራይ ክልል ያወደማቸውን አየር ማረፊያዎች፣ ድልድዮችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ጉዳይ አላነሳም።

መንግስት በትግራይ ክልል መሰረተ ልማት እንዲቋረጥ አድርጓል ሲል የኮነነው ሪፖርቱ፤ በትግራይ ክልል ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ወጭ አድርጎ ያከናወነውን መልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ስራዎችን ክዷል።

መንግስት ርሀብን እንደ ጦር መሳሪያ እንደተጠቀመ የሚያትተው ይህ ስሁት ሰነድ በአንጻሩ መንግስት በተናጠልም ሆነ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ያደረገውን ሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦት ክዷል።

መንግስት ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ በክልሉ ከሚገኙ 92 ወረዳዎች መካከል በ78ቱ ሰብዓዊ ርዳታ እንዲደርስ ያደረገ ሲሆን ከነዚህም መካከል ከ5 ነጥብ 8 ሚሊየን ሰዎች ተጠቃሚ አድርግል።

ከቀረበው ሰብዓዊ ርዳታ መካከልም የኢትዮጵያ መንግስት 70 በመቶ ቀሪው ደግሞ በዓለም አቀፍ አጋሮች የተሸፈ ነበር። ይህ ዕውነት ግን ተደብቋል። በሌላ በኩል አሸባሪው ቡድን ሰብዓዊ ርዳታ እንዳይደርስ በተደጋጋሚ ማስተጓጎሉን በማለፍ ክህደቱን አሳይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም