የመከላከያ ሰራዊቱን በሀሰት ሪፖርት ከመወንጀል ጀርባ ያለው የኢትዮጵያ ጠላቶች አደገኛ አሻጥር!

123

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን ከፋፍሎ የማዳከም ራዕይን ይዞ ከተመሰረተ ጀምሮ ላለፉት አራት አስርታት የኢትዮጵያን አንድነት የሚከፋፍሉ በርካታ ሴራዎችን ሲተገብር ቆይቷል፡፡

በተለይ ጠንካራና ኢትዮጵያን ያስቀጥላሉ የተባሉ ተቋማትን እንደ ምስጥ ከውስጥ በማዳከም የይስሙላ ስም ብቻ ይዘው እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡

አሸባሪው ህወሃት ኢትዮጵያን በመራባቸው 27 ዓመታት ከፍተኛ የማዳካም ሴራ ከፈጸመባቸው ተቋማት መካከል ደግሞ መከላከያን ጨምሮ የጸጥታ ተቋማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የሽብር ቡድኑ አመራሮች የአገር መከላከያ ሰራዊትንና የጸጥታ ተቋማትን ቁልፍ ቦታዎችን በመቆጣጠር ኢትዮጵያን በማይመጥን መልኩ ተቋሙን በማደራጀት ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር ተቀናጅተው አገርን ሲያዳክሙ ቆይተዋል፡፡

እስከውጭ አገራት ድረስ የተሳሰረ የዘረፋ ሰንሰለት ዘርግተውም አደገኛ የውንብድና ስራ ሲያከናውኑም ነበር።

በዚህም ኢትዮጵያውያን አገራቸው ያላንትን ሃብት መጠቀም ቀርቶ በቅጡ እንኳን እንዳይገነዘቡ አድርገዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ አጠቃላይ አካሄድ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች እጅጉን የተመቸና ዓላማቸውን ለማሳካት በር የከፈተ ነበር፡፡

በተለይ ደካማና ያልተደራጀ የጸጥታ መዋቅርና አንድነቱ የተሸረሸረ ህዝብ ለመፍጠር የሄደበት ርቀት በኢትዮጵያ ጠላቶች ፊት ሞግስን እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡

በዚህም የአሸባሪ ቡድኑ አመራሮች የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ምሽግ የሆነውን የመከላከያ ሰራዊት ዩኒፎርም እንኳ በቅጡ እንዳይቀይር አድርገው ከአገር ይልቅ ፓርቲን አስቅድመው ሰርተዋል፡፡

ሰራዊቱ ኢትዮጵያ የሚለውን ታላቅ ስም ወደ ጎን ትቶ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተሰኘ የዘረፋ ምሽግ እንዲጠብቅ ሰነድ በመቅረጽ ጭምር ሰርተዋል፤ በጀግንነት ታላቅ ስም ያላትን ኢትዮጵያን ከፓርቲ በታች አድርገዋት ቆይተዋል፡፡

የዚህ ሁሉ አሻጥር ዋነኛ ዓላማ የተዳከመችና አንድነቷ የላላ ኢትዮጵያን በመፍጠር አገር ማፍረስ መሆኑ እሙን ነው፡፡

የሽብር ቡድኑ የማዳከም በትሮች በተለይ በመከላከያ ሰራዊት ላይ እጅጉን የበረቱ እንደነበሩ የሚገለጽ ሲሆን፤ አየር ኃይሉም ቢሆን በአንድ አከባቢ ሰዎች የተደራጀ የይስሙላ ተቋም አንደነበር ነው የሚነገረው፡፡

በዚህም በርካታ የሰራዊቱ አባላት ከግዳጅ ቀጠና እና ከስልጠና ይጠፉ እንደነበርም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በኢትዮጵያ የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎም መንግስት ቅድሚያ ሰጥቶ የተሳካ ሪፎርም ካከናወነባቸው ተቋማት መካከል የመከላከያ ሚኒስቴር ተጠቃሽ ነው፡፡

በዚህም የመከላከያ ሰራዊቱ በአዲስ የግንባታ ስትራቴጂ ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ እንዲዋቀር ተደረገ፡፡  

ነገር ግን ሰራዊቱም ከፓርቲ ጠባቂነት የአትዮጵያ የሉዓላዊነት ምሽግ አድርጎ የማደራጀቱ ስራ በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ባለበት ወቅት “ይቺ ጥሬ ካደረች አትቆረጠምም”  በሚል የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጥላቶች አሸባሪው ህወሃትን በመጋለብ አገር የማተራመስ ስራቸውን በሁሉም አቅጣጫ ተያያዙት፡፡

የመንግስት የለውጥ ስራዎች እንዲኮላሹም በኢትዮጵያ በተቀናጀ መልኩ በተከታታይ በአሸባሪው ህወሃት አጋፋሪነት ከ113 በላይ ግጭቶች እንዲከሰቱ ተደረገ፡፡

ከግጭቶቹ ጀርባ ያለው ዋነኛ ዓላማ መንግስት የጀመረውን የለውጥ ስራ በመተው የግጭት እሳት ማጥፋት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ማዋከብ ነው፡፡

ይህ የፖለቲካና አገር የማፍረስ አሻጥር በኢትዮጵያ ጠላቶች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን በተደራጀ መልኩ በሚዲያ ዘመቻም የሚደገፍ ነበር፡፡

“ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል” እንዲሉ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ግጭት ቀስቅሰው የጸጥታ መዋቅሩን ትኩረት እንዲበተን የሚሰሩ የአሸባሪው ህወሃት ሃይሎች በዓለም አቀፍ ሚዲያ ተበዳይ መስለው በመቅረብ አገር የማፍረሱን አሻጥሩን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡

የመንግስትን ትኩረት አስቀይሶ አገር የማፍረሱ አሻጥር በፈለጉት መልኩ አልሳካ ሲላቸው ደግሞ የትግራይ ህዝብን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ሲጠብቅ የቆውን የመከላከያ ሰራዊት ሰሜን እዝ አባላትን በማጥቃት በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ገሀድ የወጣ አደጋ ፈጸሙ፡፡

በሰሜን እዝ የሰራዊት አባላት ላይ የተፈጸመው ጥቃት ዓለማችን ካጋጠሟት መሰል ጥቃቶች በአሰቃቂነቱና በዓይነቱ እጅግ የተለየ ሊሆን እንደሚችል አያጠራጥርም፡፡  

በወቅቱ ኢትዮጵያ ከነበራት ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ክምችት መካከል ከ80 በመቶ በላይ በሰሜን እዝ የነበረ ሲሆን፤ የጥቃቱ ዋነኛ ዓላማም ኢትዮጵያን ከጦር መሳሪያ ውጭ በማድረግ እንደፈለጉ እጇን መጠምዘዝ ነው፡፡

አሸባሪው ህወሃት በሰራዊቱ ላይ የፈጸመው የክህደት ጥቃት በየትኛውም የምእራባዊያን አገራት ተከስቶ ቢሆን ኖሮ ዓለም በአንድ እግሯ ትቆም እንደነበር እሙን ነው፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ ጠላቶች በራሳቸው ላይ ቢከሰት ፈጽሞ ሊታገሱት የማይችሉትን ጉዳይ ኢትዮጵያ እንድትሸከመው ፈረዱባት፤ መንግስት ችግሩን በውይይት መፍታት አለበት ሲሉም የሰላም ጠበቃ መስለው ቀረቡ፡፡

አንዳንዶቹ ደግሞ አይናቸውን በጨው በማጠብ የችግሩ ሁሉ መንስኤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በማድረግ ፈርደ ገምድል አካሄዳቸውን በግልጽ ጀመሩ፡፡

ይህ ሁሉ ሴራ በኢትዮጵያዊያን የተባባረ ክንድ መክሸፉን ተከትሎም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለም አቀፍ ተልዕኮዎች ጭምር መልካም ስም ያለውን የመከላከያ ሰራዊት በሃሰት ሪፖርት የማጠልሸት ዘመቻ ጀምረዋል፡፡

በቀጣይ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ይዘውት ከሚነሱት ፕሮጀክት መካከል ዋነኛው የሰራዊቱን "ሰብዓዊ መብት ጥሷል" በሚል የሃሰት ውንጀላ ስሙን  ማጠልሸት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

ነገር ግን የመከላከያ ሰራዊቱ ሰብዓዊነትና ህዝባዊነት መገለጫው መሆኑን ወዳጆች ብቻ ሳይሆኑ እጃቸውን ለሰራዊቱ የሰጡ ጠላቶችም ምስክር ናቸው፡፡

በመከላከያው ላይ የተጀመረው ዘመቻ ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲሄዱበት የነበረው ሴራ አካል ሲሆን ዓላማውም ኢትዮጵያዊያን “የኔ” ብለው የሚመኩበትን የመከላከያ ሰራዊት በማሸማቀቅ ኢትዮጵያን ማዳከም ብሎም ማፍረስ ነው፡፡

እነዚህ ኃይሎች አሸባሪው ህወሃት በጥፋት ተልኮው የገፋ ሲመስላቸው ዝም በማለት፤ የመከላከያ ሰራዊቱ የአገር ህልውናን የመጠበቅ ስራውን ሲጀምር ደግሞ በተደራጀ መልኩ በመጮኸ ኢትዮጵያን ደጋግመው እያደሟት ይገኛሉ፡፡

ይህን ዓላማቸውን እውን ለማድረግ ደግሞ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ከሚል ሽፋን ጀምሮ በተቀናጀ መልኩ የዓለም አቀፍ ተቋማትንና ሚዲያዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን፤ በረብጣ ዶላሮች የሚገዙ የአንዳንድ ምእራባዊያን አገራት ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶችም ከወዲሁ የፕሮጀክቱ አካል ለመሆን እየተሯሯጡ ነው፡፡

እጅግ የሚያስገርመው ነገር ደግሞ መከላከያውን በሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊከሱ የሚሞክሩ ኃይሎች አሸባሪ ቡድኑ በገሃድ ለትግራይ ህዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚውል ነዳጅ ሲዘርፍ በቅጡ እንኳ ማውገዝ አለመቻላቸው ነው፡፡

ይህም የኢትዮጵያ የመጨረሻ ምሽግ የሆነውን ሰራዊት ለማፍረስ ምን ያህል የተደራጀ ሴራ እንደሚከተሉ አመላካች ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጠላቶች ያልተገነዘቡት ነገር ቢኖር በዓለም አቀፍ ተቋማት ስም ይሁን በየትኛውም የተደራጀ አግባብ ሰራዊቱ ላይ የሚከፈት ስም የማጥፋት ዘመቻ የመላ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ከመቸውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን በመጠበቅ በሁሉም ግንባሮች የተቃጡ አገር የማፍረስ ሴራዎችን ነቅተን መከላከል አለብን፡፡

የመከላከያ ሰራዊቱ ቀን ከሌት ለአገሩ ህለውና እየተዋደቀ እንደሚገኝ ሁሉ ደጀኑ ህዝብ "እኔም ለአገሬ ወታደር ነኝ" በሚል የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን እቅድ ማክሸፍ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ የሚገጥሟትን ፈተናዎች በድል ተሻግራ ዳግም የመላ ጥቁር ህዝቦች  አብነት እንደምትሆን አያጠራጥርም፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም