ቀጥታ፡

ቡድኑ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ በማራመዳችን የሰብአዊ ጉዳት አድርሶብናል- የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት

ሶዶ መስከረም 11/2014 (ኢዜአ) ... አሸባሪው ህወሓት አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ በማራመዳቸው ለከፋ ሰብአዊ ጉዳት ይዳርጋቸው እንደነበር በወላይታ ሶዶ ዞን የሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት ገለጹ፡፡

የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባላቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት ዜጎችን በግፍ አገዛዝ ያኖረው የሽብር ቡድኑ ዛሬም የስልጣን ጥሙን ለማርካት የትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት እየማገደ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።

አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ቆይታው አማራጭ የፖለቲካ ሀሳብ በመያዛቸው ብቻ ያለምንም ጥፋት በእስር ከማንገላታት ባለፈ በፈጸመባቸው የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለስነ ልቦና ጉዳት እንደዳረጋቸው የፓርቲ አመራርና አባላቱ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ወልዴ ዳና አማራጭ የፖለቲካ እሳቤ በመያዛቸው ምክንያት ለበርካታ ዓመታት ከቤተሰባቸው ጀምሮ ማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳደረሰባቸው ገልፀዋል፡፡

ለሰባት ዓመታት በተለያዩ እስር ቤቶች መቆየታቸውን ገልጸው በቃላት የማይገለጽ ጭካኔና የሰብአዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል፡፡

ለኢትዮጵያ መፍረስ አቅዶና አልሞ የተደራጀው ቡድኑ ሲያራምደው የነበረው የዘርና የብሄር ፖለቲካ ለሴራው መገልገያነት የረዳው መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ ታሪካዊ ጠላቶች ቡድኑ ዓላማቸውን እንዲያስፈጽም የሚጋልቡት መሆኑን ባለፉት ዓመታት ባከናወነው ተግባር በግልጽ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን "ካለኔ ኢትዮጵያ አትቀጥልም” በሚል ሲመፃደቅና ከታሪካዊ ጠላቶቿ ጋር በማበር ሊያፈራርሳት ሲጥር የቆየ ቡድን መሆኑን አንስተዋል፡፡

"ቡድኑ እቅዱ ራሱን ይዞ ወደ ተመኘው ሲኦል ይሸኘዋል እንጂ ኢትዮጵያ በልጆቿ አንድነትና የተባበረ ክንድ ነጻነቷንና ሉዓላዊነቷን አስከብራ ትቀጥላለች " ብለዋል።

"ቡድኑ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም የሚጠቀመው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የማያልቅበት በመሆኑ የትግራይ ህዝብ ሴራውን በመረዳት ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል" ሲሉም አመልክተዋል ።

"ቡድኑ ህዝብን መንግስት ላይ ለማሳመፅ ከሚጠቀምባቸው ሴራዎች አንዱ  በየአካባቢው የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር ማድረግ መሆኑን ሰሞኑን ባወጣው የጥፋት ሰነድ ማረጋገጡን የጠቆሙት ሀላፊው ህዝቡ የውስጥ አንድነቱን በመጠበቅ ቡድኑን ለአንዴና ለመጨረሻ የማስወገድ ትግሉን ማስቀጠል እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡  

በኢዜማ የወላይታ ዞን ምክር ቤት አባልና የዳሞት ፑላሳ ወረዳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ክንፈ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ በማራመዳቸው ተቃዋሚ የሚል መጠሪያ እንደሰጣቸውና በዚህም ለከፋ የሰብአዊ ጉዳት እንደዳረጋቸው አስታውሰዋል፡፡

ያለጥፋት ከስራ መባረርን ጨምሮ  በአከባቢው እንዲሸማቀቁ የሚያደርግ አካል በመመደብ ከማህበራዊ ህይወት መገለላቸውንና ቤተሰቦቻቸውም የጉዳቱ ሰለባ እንዲሆኑ ያደረገ ቡድን መሆኑን ተናግረዋል።

"አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ዘመኑ  ከግለሰብ ጀምሮ በዘረጋው የመቅጫ በትር ኢትዮጵያዊያንን ለከፋ ስቃይ ሲዳርግ ቆይቷል" ሲሉም አመልክተዋል፡፡

ቡድኑ ያራምደው የነበረው የዘር ፖለቲካ ኢትዮጵያዊያንን ለመቅጣትና ሀገርን ለመበታተን የታቀደ ፕሮጄክት መሆኑን ጠቁመው  "አሁን ላይ ግልጽ ጦርነት በመክፈት  ራሱን መንግስት ብሎ መጥራቱ  ይህንኑ የሚያሳይ ነው " ሲሉም አክለዋል ።

ቡድኑ ህዝቡን በዘር፣ በብሔርና በፖለቲካ አመለካከት በመከፋፈል በህዝቦች መካከል ልዩነት ፈጥሮ ሲያሰቃይ መቆየቱን ተናግረዋል።

በመሆኑም በተለይ የትግራይ ተወላጆች ቡድኑ ሀገር ለማፍረስ የያዘውን ሴራ ለማሳካት ዳግም የከፈተውን ጦርነት አሻፈረኝ በማለት ከመንግሥት ጎን ሊቆሙ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም