ኮሚሽኑ በቡራዩና በአካባቢዋ በተፈጸመ ጥቃት የተሰማውን ሐዘን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በቡራዩና በአካባቢዋ በተፈጸመ ጥቃት የተሰማውን ሐዘን ገለጸ
አዲስአበባ 10/2011 የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በቡራዩና በአካባቢዋ በተፈጸመ ጥቃት የተሰማውን ሀዘን ገልጿል። የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማህማት በአዲስ አበባ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው ቡራዩ ከተማና አካባቢዋ የብዙዎችን ህይወት የቀጠፈ፣ለጉዳት የዳረገውና ያፈናቀለው ጥቃት ከፍተኛ ሀዘንና ድንጋጤ ማስከተሉን ገልጸዋል። ድርጊቱን የህብረቱ ኮሚሽን በእጅጉ እንደሚያወግዘው የገለፁት ሊቀመንበሩ የአፍሪካ ህብረትም የኢትዮጵያዊያንን ሀዘን እንደሚጋራ አስታውቀዋል። የአፍሪካ ህብረት በተፈጠረው ክስተት የተሰማውን ከባድ ሀዘን ለኢትዮጵያ መንግስትና ለተጎጂ ቤተሰቦች መላኩን ጠቁመው ህብረቱ ከተጎዱት ጎን እንደሚቆምና ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል። ይህን መሰሉን ድርጊት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በአንድነት በመቆም የህግ የበላይነት እንዲከበር የሚያደርጉትን ጥረት የበለጠ እንዲገፉበት መነሳሳት የሚፈጥር መሆኑን ሊቀመንበሩ አመላክተዋል። የአፍሪካ ህብረት በኢትዮጵያ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት እንደሚደግፍና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሚመራው መንግስት ጋር እንደሚቆም አረጋግጠዋል።