ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ሪፖርት ለሰብዓዊ መብት ከመቆርቆር ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳ ያነገበና የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም የተዘጋጀ ሪፖርት ነው ብሎ መንግስት ያምናል - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ሪፖርት ለሰብዓዊ መብት ከመቆርቆር ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳ ያነገበና የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም የተዘጋጀ ሪፖርት ነው ብሎ መንግስት ያምናል
መስከረም 11 ቀን 2015 (ኢዜአ)ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ሪፖርት ለሰብዓዊ መብት ከመቆርቆር ሳይሆን የፖለቲካ አጀንዳ ያነገበና የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም የተዘጋጀ ሪፖርት ነው ብሎ መንግስት ያምናል።
የወንጀል ተጠያቂነትን ለማስፈን በፍትህ ሚኒስቴርና በፌዴራል ፖሊስ የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫው የተከናወኑ የምርመራ ስራዎች የት እንደደረሱ እንዲሁም የተመድ የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ያቋቋመውን የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርትን የተመለከተ ነው።
የግብረ ኃይሉ ፅህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ታደሰ ካሳ ከሰሞኑ የተመድ የሰብዓዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን ለ9 ወራት ሲያጠና የቆየውን የጥናት ሪፖርት ይፋ ማድረጉን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስትም ከኮሚሽኑ መቋቋም ጀምሮ መቃወሙን ገልፀዋል።መከላከያ መቀሌ ሲገባ የከባድ መሳሪያ ድብደባና የንፁሃን ጥቃት፣የቆቦና የጭና ጭፍጨፋ፣በ2014 ጥር ወር ደደቢት ላይ የድሮን ድብደባ ተፈጽሟል በሚል ምርመራ እንዳደረገ ገልፀዋል።
በውጤቱም የኢትዮጵያ መንግስት ርሀብን እንደ ጦር መሳሪያ መጠቀሙን፣ ለተፈጸሙ ፆታዊ ጥቃትና የንፁሃን ጥቃት መንግስት ተጠያቂ ያደረገ ድምዳሜ ነው ብለዋል።ጥናቱ በጣም ቁንፅል ስዕል የሚሰጥ መሆኑንም አንስተዋል።
የተመድ የሰብዓዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን አጠናሁት ያለው ጥናት መሰረታዊ የጥናት እሳቤዎችንና የአጠናን ዘዴን ያልተከተለ ከመሆኑም በተጨማሪ ገለልተኝነት የጎደለው መሆኑን ገልጸዋል።
ጥናቱ በመረጃ አሰባሰብ ስርዓትም እንዲሁ ጉድለት ያለበትና ታማኝነቱን ጥያቄ ውስጥ የከተተ ጥናት ነው ብለዋል።መንግስት ኮሚሽኑ ያዘጋጀው ሪፖርት ለሰብዓዊ መብት ከመቆርቆር ሳይሆን ሌላ የፖለቲካ አጀንዳ ያነገበና የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈፀሚያ የሆነ ሪፖርት ነው ብሎ ያምናል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ ፈቃዱ ፀጋ በበኩላቸው መንግስት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በአጠቃላይ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ መደረጉንና ሂደቱም እንደቀጠለ ገልፀው፣ በዚህም የወንጀል ተጠያቂነት ለማረጋገጥ ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል።በሕግ ማስከበር ሂደቱ ጀምሮ ጥፋት የፈፀሙ የሰራዊቱ አባላት በወታደራዊ ፍርድ ቤት የፍርድ ውሳኔ መሰጠቱን ገልፀዋል።
ግብረ ኃይሉ ከተቋቋመ በፊትና በኋላ በጦርነቱም ሆነ በቤሻንጉል ክልል ጥፋት የፈፀሙ የፀጥታ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን ገልፀዋል።የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በበኩላቸው ከሕወሓት ሁለተኛ ዙር ወረራ በኋላ የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ውስጥ በተቋቋመ ንዑስ የምርመራና ክስ ኮሚቴ በአማራና አፋር የደረሱ ጥፋቶችን ምርመራ ማከናወኑን ገልፀዋል።
በዚህም ከ26 ሺህ በላይ መኖሪያ ቤቶች መጎዳታቸውን፣ 28 ሺህ ሱቆች፣ 2,500 ጤና ጣቢያዎች መውደማቸውን ገልፀው፣ በአማራ ክልል ከ9 ሺህ በአፋር ከ500 በላይ ምስክሮች ተገኝተዋል ብለዋል።ምርመራው በሌሎች አካባቢዎችም እንደተደረገ ገልጸው የመጨረሻው እንዳልሆነም ገልጸዋል።
ድርጅቱ እንደ ድርጅት ሒሳብ አወራርዳለሁ በማለት በሽብር ቡድኖቹ ሕወሓትና ሸኔ 2,831 በጦርነት ባልተሳተፉ ሰዎች ላይ ከፍርድ ውጭ የጅምላ ግድያ መፈጸሙን ገልጸዋል።ለአብነትም ቆቦ፣ ጭና፣ አንፆኪያ ገምዛና ሌሎች አካባቢዎችን ጠቅሰዋል።ይህን ወንጀል የፈፀሙትም በሕወሓት አመራሮቾ ትዕዛዝ ነው ብለዋል።
የወንጀሉ አፈፃፀም በአሰቃቂ ደረጃ የሚገለጽ እንደሆነና አስከሬናቸውም ሳይነሳ መቆየቱን ገልፀው፣ ዓለማውም ማህበረሰቡን ማዋረድ የሚል ግብ እንደነበረው ተናግረዋል።
አገዳደላቸውንም በተመለከተ ዓይኖቻቸውን በማውጣት፣ ከአስከሬን ጋር በማስተኛት፣ የ15 ወር ህፃን ከእናት ነጥቆ በጫማ ረግጦ በመግደልና መሰል ጭካኔ በተሞላባቸው መንገድ ተገድለዋል።በርካታ የቆሰሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ከጤና ጣቢያ በመውሰድ ያለፍርድ መግደልንም እንደሚያካትት ተገልጿል።
ከኢትዮጵያዊ እሴት ባፈነገጠ መልኩ በቡድን፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ የ80 ዓመት መነኩሲት፣ የ9 ወር እርጉዝ፣ እና ሌሎችንም በጭፍን ጥላቻ በመነሳሳት ከ2,200 በላይ ሴቶች የአስገድዶ መድፈር፤ አራስ ሴት የተገደለችበት፣ ኮምቦልቻ ባሏን ገድለው አንገቷን ቆርጠው የደፈሩበት፣ለ7 በቡድን ተደፍራ የሞተችበት፣በሀይማኖት አባት ቄስ ፊት ባለቤታቸው የደፈሩበት ክስተቶች እንደነበሩ አንስተዋል።
በወንዶች ላይም የተደፈሩ ሰዎች ሲኖሩ ሐይቅ ከተማ ላይ የ13 ዓመት ልጅ ለሶስት በመሆን የደፈሩበትንም አጋጣሚ አንስተዋል።
በደረሰባቸው ጾታዊ ጥቃት ምክንያት ህይወታቸውን ያጡ እንዳሉ እና አብዛኞቹም እስካሁን ከጉዳታቸው ያላገገሙና ለፊስቱላ ተዳርገው አሁንም ከሕክምና ያላገገሙ መኖራቸው ተጠቅሷል።በቡድን የመደፈር ጥቃት ከደረሰባቸው መካከልም አካል ጉዳተኞች፣ ማየት የተሳናቸው፣ስደተኞችና ተፈናቃዮች እንደሚገኙበትም ተገልጿል።ቡድኑ የተበላሸ ምግብ እና ቆሻሻ ውሃ እንዲጠጡ ማስገደድን ጨምሮ በርካታ ግፎችና ወንጀሎች መፈጸሙን ገልጸዋል።
ቡድኑ በፈጸመው የንብረት ዘረፋ እና ውድመት ላይ የትግራይ ክልል ንግድና ኢኮኖሚ ቢሮ በመሪነት እንደተሳተፈ እና ኮሚቴ በማዋቀር ጭምር መፈጸሙን ገልፀዋል።የዘረፉ ቡድኑ የሚመራው በአሸባሪው ቡድኑ መሪ እንደሆነ ገልፀው መዝረፍ ያልቻሉትን እንዲወድም ተደርጓል፣ የጥላቻ ፅሁፎች እንደተፃፉም ገልፀዋል።
የማህበረሰቡን ሞራል ለመንካት በማሰብም የመንግስት ተቋማትና ሆቴሎችን እንደ ሽንት ቤት ሲጠቀሙ ነበር ተብሏል።