ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አዳዲስ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ተግባራዊ ሊሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አዳዲስ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች ተግባራዊ ሊሆኑ ነው
መስከረም 11/2015/ኢዜአ/ ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አዳዲስ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታገል ቀኑብህ ለኢዜአ እንዳሉት በ8100A አጭር ፅሁፍ መልዕክት የተጀመረው የረዥም ጊዜ ገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮጀክት ይቀጥላል።
ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የቴምብር ማህበር አባል በመሆኗ በህዳሴ ግድብ ስምና ምስል ቴምብር በማተም የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራና ገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት እንደሚጀመር ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሰረታዊ መረጃዎችን የያዙ ደብተሮችን ለገበያ ማቅረብን ጨምሮ አዳዲስ የጊቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችም ተግባራዊ እንደሚሆኑ ነው የገለጹት።
ደብተሮቹ የኢትዮጵያውያን የአንድነት አሻራ ያረፈበትን የህዳሴ ግድብ መሰረታዊ መረጃዎች ትውልድ እያወቀ እንዲሄድ ያስችላሉ ብለዋል።
ግድቡ ከብርሃን ወደ ጨለማ ለመሻገር፣ ለኢንዱስትሪ ሃይል አቅርቦትና ለሌሎች የምጣኔ ሃብት እድገት ትልቅ ተስፋ እንደተጣለበትም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጉዞ ትልቅ ሚና የሚኖረው የህዳሴ ግድብ ለፍጻሜ እንዲበቃ ኢትዮጵያውያን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በእውቀት፣ በገንዘብና በሃሳብ ብርቱ ተሳትፎ እያደረጉ ናቸው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሶስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ መንግስት መግለጹ ይታወሳል።