የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት ከቤተሰቦቻችን ፊት አስገድደው ደፍረውናል--የቡድኑ የጭካኔ ድርጊት ሰለባዎች

ጎንደር መስከረም 11/2015  (ኢዜአ) "የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት ከሰው ባህሪ ወጥተው በቤተሰቦቻችን ፊት በቡድን አስገድደው በመድፈር በሕክምና ለማይድን በሽታ ዳርገውናል" ሲሉ በሰሜን ጎንደር ዞን ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ሴቶች ገለጹ።

የሽብር ቡድኑ አባላት በዞኑ በርካታ ሴቶችን አስገድደው በመድፈር በዓለም አቀፍ ህግ ተጠያዊ የሚያደርግና ታሪክ የማይረሳው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መፈፀማቸው ተገልጿል።

"የቡድን አባላት ፀያፍ ንግግርና ድርጊታቸው ከኢትዮጵያውያን እምነት፣ ባህልና ወግ ውጭ ነው'' ያሉት በዞኑ በቡድን አባላቱ የተደፈሩ አንዲት እናት ናቸው።

የሰባት ወንድ ልጆች እናትና የ57 ዓምት እድሜ እንዳላቸው የገለጹት እኚህ እናት በቡድን አባላት የተፈፀመባቸውን የጭካኔ ተግባር የተናገሩት ጉልበታቸው እየተንቀጠቀጠ፣ ዓይኖቻቸው እምባ እየቋጠሩና አንደበታቸው እየተሳሰረ ነው።

የሽብር ቡድን አባላት አካባቢውን በወረራ በያዙበት ወቅት ወደ መኖሪያ ቤታቸው ደጋግመው እየመጡ አስገድደው ምግብ ሲመገቡ እንደነበረም ተናግረዋል።

"ቤታችን ድረስ መጥተው እናንተ አማራዎች የእኛን እናትና አባት፣ ወንድም፣ እህቶቻችንና ልጆቻችንን ገድላችዋል" እያሉ ከማስፈራራት ባለፈ በፀያፍ ንግግር ይሰድቧቸው እንደነበረም አስታውሰዋል።

"የጥቃት ድርጊት እንዳይፈፅሙብኝ የእምባ ጎርፍ እያፈሰስኩ በተማፅኖ ለመንኳቸው፤ ለመከላከል በምችለው አቅሜ ሁሉ ተፍጨረጨርኩ ግን እነሱ የሚሰሙበት ጀሮ፣ የማሰቢያ አዕምሮ የላቸውም፤ እኔም አልቻልኩም ይባስ ብለው መሃል አናቴን በቢለዋ ወጉኝ" ሲሉም የተፈጸመባቸውን የጭካኔ ድርጊት ይገልጻሉ።

"ከጭካኔ ድርጊታቸው ያልተቆጠቡት የቡድን አባላት ከቤተሰቦቼ ፊት ከሰው ባህሪ ባፈነገጠ መንገድ እራሴን እስክስት ድረስ ለአራት እየተፈራረቁ ደፍረውኛል'' ሲሉም የጭካኔ ድርጊታቸውን ተናግረዋል።

በተፈፀመባቸው መደፈር ከፍተኛ ደም እንደፈሰሳቸው የተመለከተው ወንድማቸው "ጨርሰው እንዳይገሏት" በሚል እሳቤ ከቤት አውጥቶ ለሦስት ቀናት ጫካ ውስጥ ደብቆ እንዳቆያቸው ገልፀዋል።

ራሳቸውን ያወቁት ከቀናት ቆይታ በኋላ እንደሆነ የሚናገሩት እኚህ እናት፣ "በወቅቱ የነበረውን ህመም፣ ስቃይና በጫካ መንገላታቱን ሲያስታውሱ "ሞትን መርጬ ነብር" ይላሉ።  

በአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት በተፈጸመባቸው የአስገድዶ መደፈር ለፌስቱላ፣ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ፣ እና ለደም ግፊት በሽታ መዳረጋቸውን ሲናገሩም በእንባ እየቀደማቸው ነው።

ጥቃት ከተፈጸመባቸው በኋላ ባህር ዳር ከተማ ድረስ መጥተው ሕክምና ቢያገኙም አሁንም ከፍተኛ የሕመም ስሜት እንዳላቸው ገልፀዋል።

"ከምንም በላይ የደረሰብኝን የስነ ልቦና ስብራት መቋቋም አልቻልኩም" ይላሉ። የብዙዎች አጀንዳና መሳለቂያ አልሆንም በሚል ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው መመለስ እንዳልቻሉም ነው ያስረዱት።

"ህወሓት ህዝብን ለማሰቃየት የመጣ፣ ዘራፊ፣ ሌባና የባለጌዎች ቡድን በመሆኑ በእኔ ላይ የተፈፀመው በሌሎች ሴቶች ላይ እንዳይፈፀም አሸባሪወን ህወሓት ተባብሮ ማጥፋት ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።

እኚህ እናት እንዳሉት ሁለት ልጆቻቸው ቡድኑን ለመፋለም የጸጥታ አካላትን ተቀላቅለው ወደ ግንባር ዘምተዋል። እርሳቸውም አቅምና እድሜ ቢፈቅድላቸው ቡድኑን ለመታገል ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

"አሁን ላይ በሽብር ቡድን ሃብት ንብረቴ ተዘርፎ፣ ከመኖሪያ ቀዬ ተፈናቅዬ፣ ልጆቼ ተበትነውና ሰርቼ እንዳልበላም ተደራራቢ በሽታ ያለብኝ በመሆኑ ተገቢ ድጋፍ ቢደረግልኝ'' ሲሉ ጠይቀዋል።

ሌላዋ የሰሜን ጎንደር ዞን ነዋሪና በህወሓት የሽብር ቡድን አባላት ተገዳ የመደፈር ድርጊት የተፈፀመባት የ25 ዓመት ወጣት በበኩሏ፣ "የቡድን አባላት በሰው አምሳል የቆሙ ነገር ግን የሰው ባህሪና እሳቤ የሌላቸው ናቸው" በማለት ነው የገለጸቻቸው።

የቡድን አባላት አካባቢውን በወረሩበት ወቅት ስምንት ሆነው ወደ መኖሪያ ቤቷ በመምጣት ያገኙትን የሚበላ ነገር ሁሉ እንደበሉ ታስታውሳለች።

ከቤቷ ተቀምጠው "እናንተ አማራዎች የትግራይን ህዝብ ልታጠፉ ነው? ወንዱ ሁሉ የት ሂዶ ነው? እኛን ሊዋጋ ሄዶ ነው?" አያሉ በዛቻ ስሜት ይናገሩ እንደነበር ተናግራለች።

በአጋጣሚ በአካባቢው የነበረ አንድ የአጎቷን ልጅ በጥይት ተኩሰው ትክሻውን እንዳቆሰሉት የገለጸችው ወጣቷ፣ "የእሱን መቁሰል ሳይ ደነገጥኩ" በማለት የወቅቱን የጭካኔ ድርጊት አስታውሳለች።

ወደቤት ከገቡት የቡድኑ አባላት መካከል ቤት ውስጥ የቀሩት ሁለቱ እየተፈራረቁ እንደደፈሯት በቁጭት ትናገራለች።

በተፈጸመባት የጭካኔ ድርጊት ከፍተኛ የደም መፍሰስ ችግር አጋጥሟት እንደነበረም ገልጻለች።

በችግር ውስጥም ሆና የባሰ እንዳይመጣ በማለት ሁለት ሕጻናትን በመያዝ ለሦስት ሳምንት በጫካ  ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ማሳለፏን  አስረድታለች።

በቡድኑ አባላት ከተደፈረች በኋላ ተገቢውን ሕክምና በማግኘት ጤንነቷ መስተካከሉን የገለጸቸው ወጣቷ፣ "የአካባቢው ማህበረሰብ 'የጁንታ ውዝፍ' ይለኛል በማለት ተመልሼ ወደአካባቢዬ መሄድ አለቻልኩም"  ብላለች።

"የህወሓት የሽብር ቡድን አረመኔና የሰይጣንን ባህሪ የተላበሱ ጨካኞች ስብስብ በመሆናቸው ሁሉም ተረባርቦ ሊያጠፋቸው" ይገባል።

የአማራ ሴቶች ማህበር የሰሜን ጎንደር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሰብለ ባየህ በበኩላቸው፣ "የህወሓት የሽብር ቡድን ያልፈፀመው በደል አለ ብሎ ማለት አይቻልም" ብለዋል።

በመንግስትና ግለሰቦች ንብረት ከፈጸመው ዘርፋና ውድመት ባለፈ ንፁሃን ሰዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ጭምር መግደሉን ገልጸዋል።

ይህ ሳይበቃው አካባቢውን በወረራ ይዞ በቆየበት ወቅት ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር ለበሽታና ለስነ ልቦና ችግር መዳረጉን ነው ያመለከቱት።

በእዚህም የቡድኑ አባላት በዓለም አቀፍ ህግ ተጠያዊ የሚያደርግና ታሪክ የማይረሳው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት መፈፀማቸው አስረድተዋል።

ሃላፊዋ እንዳሉት በዞኑ በርካታ ሴቶች የተደፈሩ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ጥቃት የተፈፀመባቸው 67 ሴቶች ብቻ ችግራቸውን በድፍረት በማሳወቅ ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል።

የጥቃቱ ሰላባ የሆኑት በርካቶቹ እንደሆኑ ያነሱት ወይዘሮ ሰብለ፤ የህብረሰቡን ተፅኖ በመፍራት እራሳቸውን የደበቁ እንዳሉም ተናግረዋል።

"የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት የ11 ዓመት ህፃንን ጨምሮ የካህናትን ሚስት ጭምር በመድፈር ለህዝብ ያላቸውን የከፋ ጥላቻ አሳይተዋል" ብለዋል።

በቡድኑ አባላት ጉዳት ለደረሰባቸው አቅም በፈቀደ የህክምናና ሌሎች ድጋፎች እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ነገር ግን ከደረሰባቸው በደልና ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው ከመኖራቸው አንፃር አሁንም ሰፊ ድጋፍ እንደሚፈልጉ አመልክተዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም