በዞኑ በዝናብ አጠር አካባቢዎች ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የምግብና የገበያ ሰብሎች እየለሙ ነው

14

ጎንደር፤ መስከረም 11/2015 (ኢዜአ)፡ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በዝናብ አጠር አካባቢዎች ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የምግብና የገበያ ሰብሎችን በ11 ሺህ ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ የዘር ብዜትና የማስፋት ስራ እያከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በዞኑ በምዕራብ በለሳ ወረዳ በምርምር የወጡ የማሾና የማሽላ ዝርያዎች የዘር ብዜትና የማስፋት ስራ ላይ የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ በጉብኝቱ ላይ እንዳሉት በዞኑ  በሚገኙ  አምስት ወረዳዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች በምግብ ራሳቸውን ከማስቻል ባለፈ ለገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ታስቦ የዘር በዜቱ  እየተካሄደ ነው።

 በምዕራብ በለሳ ወረዳ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዝ "መልካም" የተባለ የማሽላ ዝርያ በ70 ሄክታር ላይ እየተባዛ መሆኑን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በምርምር የተገኘው የማሽላ ዝርያ በሄክታር 45 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችል መሆኑን አመልክተው፤ ይህም ከአካቢው ዝርያ ጋር ሲነጻጸር በ3 እጥፍ የምርት ጭማሬ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

"የማሽላ ሰብሉ በ200 አርሶ አደሮች ማሳ ላይ በኩታ ገጠም እርሻ እየለማ ነው" ያሉት ሃላፊው፤  ዝርያው ባጭር ጊዜ  የሚደርስና በሽታን መቋቋም የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በ2014/15 ምርት ዘመን በመደበኛውና በኤክስቴንሽን ከለማው 24 ሺህ ሄክታር የማሾ ሰብል 192 ሺህ ኩንታል ለውጪ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።  

 11 ሺህ ሄክታር ያህሉ የማሾ ሰብል የዝናብ አጠር በሆኑት አምሰቱ ወረዳዎች እየተመረተ መሆኑን ጠቁመው፤ ወረዳዎቹ በምግብ ራስን ከመቻል ባሻገር ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ በእቅድ ተይዞ  እየተሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምንተስኖት ወርቁ በበኩላቸው በምርምር የወጡ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ማዕከሉ ለዝናብ አጠር አካባቢዎች ተስማሚ የሆኑ የማሾና ''መልካም' የተባለ የማሽላ ዝርያ በምርምር በማፍለቅ ከሰርቶ ማሳያ ወደ አርሶአሩ ማሳ ሽግግር በማድረግ በስፋት እንዲለሙ ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መልካም የተባለውን ምርጥ የማሽላ ዝርያ በኩታ ገጠም እርሻ እያለሙ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ  በምዕራብ በለሳ ወረዳ የቃላይ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ሲሳይ ታከለ ናቸው፡፡

የበለሳ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ሞላ አሰፋ በበኩላቸው የማሾ ሰብል በገበያ ተፈላጊና በዋጋ ደረጃም ከሌሎች የገበያ ሰብሎች የተሻለ በመሆኑ ባላፉት ሁለት ዓመታት በልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

በመስክ ጉብኝቱ ከዞኑ 15 ወረዳዎች የተውጣጡ አርሶ አደሮች የግብርና ባለሙያዎችና አመራሮች እንዲሁም የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከልና የጎንደር ዩንቨርሲቲ ተመራማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም