ከጥርስ ያልወጣች አገር

21

(ስውሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት "ጥናት" ሰነድ)

በአየለ ያረጋል

ታሪክን ወደኋላ...

የሺህ ዓመታት ባለታሪኳ ኢትዮጵያ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎችን ያልተጋፈጠችበት ዘመንና ሁነት የለም። ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ ጠላቶቿ ስውራዊና ገሃዳዊ ፖሊሲ ቀርጸው ኢትዮጵያን ለማጥፋት ያልፈነቀሉት ድንጋይ፣ ያልማሱት ጉድጓድ፣ ያልበጠሱት ቅጠል የለም። ኢትዮጵያ የምትባል አገር በአንዳንድ ምዕራባዊያን ዐይኖች ቂም የተያዘባት፣ በየዘመኑ የበቀል ፍላጻ የሚወረወርባት፣ የምቀኝነት አባዜ ያረፈባት ምድር ናት። የአድዋ ድል ቂም በቀል ከአገራት ጂኦ-ፖለቲካዊ ብሔራዊ ጥቅም ጋር ተዳምሮ ምዕራባዊያን ከጥንትም ጀምሮ ኢትዮጵያን እንደተፈታተኗት አሉ።

በኢትዮጵያ ላይ ሃይማኖታዊ ተልዕኮ የነበራቸው ፖርቱጋሎች ከክርስቲያን ደጋማው መንግስት ወገን ሆነው ቢያግዙም ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ ለመከፋፈል ግን አልቦዘኑም ነበር። በሌሎች የአፍሪካ አገራት እንዳደረጉት ሁሉ በሚሺነሪነት ሽፋን የምዕራብ ስውር ተልዕኮ ያነገቡ ግለሰቦች በኢትዮጵያ ምድር ተመላልሰው የሴራ አሽክላቸውን አጥምደዋል።

በዘመነ መሳፍንትም ኢትዮጵያን ከቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ለመክተት ጥረዋል። ለዚህም የዓባይ ምንጭን የመቆጣጠር ህልም ያላት ግብጽን ተጠቅመዋል። በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስትም በባሕረ ነጋሽ ባንዳ መሳፍንትን በማባበል የኢትዮጵያን መውጫ መግቢያ የባህር በሯን ለመያዝ የውጭ ሃይሎች ሰርተዋል።

በአጼ ዮሐንስ ዘመንም በአሜሪካ የጦር መኮንኖች የሚመራው የግብጽ ጦር ኢትዮጵያን በኅይል ለመውረር በተደጋጋሚ ሞክሮ ከሽፎበታል፤  በምስራቅ ኢትዮጵያ ሐረርን ወሮ የነበረው የግብጽ ጦርም በአጼ ምኒልክ ዘመን ተባሯል። ነገር ግን ከአድዋ ድል በኋላም ኢትዮጵያ ውስጥ ስውር ተልዕኳቸውን በማራመድ ኢትዮጵያዊያንን እርስ በርስ ለማጋጨት መስራታቸውን ቀጥለዋል። የአጼ ምኒልክ መንግስት ተዷክሟል በሚል ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና እንግሊዝ ኢትዮጵያን የመከፋፈል ውል (ትራይፓርታይት ትሪቲ) ተፈራርመው ነበር።

ምዕራባዊያን የልጅ ኢያሱ መንግስት ውስጥ ሴራ በመጎንጎን በሃይማኖትና በጎጥ መካፋፈል እንዲኖር በማድረግ ለምሳሌም ደም አፋሳሹ የሰገሌ ጦርነት እንዲካሄድ አድርገዋል። ከልጅ ኢያሱ ውድቀት በኋላም አጼ ሃይለስላሴ እስከነገሱበት ጊዜ ድረስ በንግስት ዘውዲቱና በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ሽኩቻና እርስ በርስ ጦርነት እንዲካሄድ ከጀርባ ሴራ ጎንጉነዋል።

ጣሊያን ከአድዋ ድል 40 ዓመታት በኋላ ዳግም ወረራ ፈጽማ በሰው ልጆች ታሪክ ከባድ ግፍ አድርሳለች። በዚህ ወቅት በምዕራባዊያን የሚመራው ሊግ ኦፍ ኔሽንም የጣሊያን የግፍ ወረራ ከማውገዝ ይልቅ ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ እንዳታስገባ አድርጓል። ፋሺስት ጣሊያ የማኪያቬሊ የከፋፍለህ ግዛት ፖሊሲ ቀርጻ ኢትዮጵያን በዘርና በሃይማኖት ለመከፋፈልና የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ፈጥራ ለመግዛት ሞክራለች።

ከኢጣሊያን መባረር በኋላ እንግሊዝ ኢትዮጵያን የሞግዚት አስትተዳደር ለማድረግ ጥራለች። በጎሳ ጦርነት እንድትዳከም ሰርታለች። በዘመናዊ የጦርና የፖለቲካ ጥበብ በተካኑ ጄኔራሎቿ በመመራት ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ በማፋጀትና መንግስትንም አማጺያንንም በማዳከም ኢትዮጵያን ወደ እንግሊዝ ግዛተ አጼ ለመጠቅለል አልመው ነበር። ኤርትራን ጨምሮ ሌሎች የቀደምት ኢትዮጵያ ግዛቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይመለሱ ብርቱ ተጋድሎ አድርገዋል። ኢትዮጵያ ግን በእሳት ተፈትና ተወጥታዋለች።

በአፄ ኅይለስላሴ መንግስት ወዳጅ የነበሩት ምዕራባዊያን ሶማሊያዊው ዜያድባሬ ኢትዮጵያን እንዲወጋ ከጀርባ አሲረዋል። ይህም ጠላትን ከጀርባ አስጣጥቆ ኢትዮጰያን ማስወጋት በደርግ ዘመነ መንግስት  ቀጥሏል። የኢትዮጵያን አገራዊ አንድነት ከሚያስጥብቁ ቡድኖች ይልቅ ተገንጣይ አስተሳሰብ ያነገቡ እንደ ሕወሃት ያሉ ሀይሎችን ለመንግስትነት እንዲበቁ በማድረግ ኢትዮጵያን የመገነጣጠል ተልዕኳቸውን ገፍተውበታል።

አሸባሪው ሕወሃትም በ1983 ዓ.ም ወደ ስልጣን ሲመጣ አስቀድሞ ተፈጻሚ ማድረግ የፈለገው ይህንኑ የአውሮፓዊያን የቀደመ ኢትዮጵያን በዘርና በቋንቋ ከፋፍሎ የመግዛት ዕቅድ ነበር። እንግሊዝ ጎሳዎችን በተለያየ ስብከት፣ ሽንገላና ግፊት በመዳፏ ለማስገባት ከፋፋይ አካሄዷን እንደ ስውር ወጥመድ ለመጠቀም ያልሄደችበት ጥግ አልነበረም።

ይህ ታሪካዊ የምዕራባዊያን ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ መልኩን ቢቀያይርም ዛሬም ድረስ አለ። በቅርቡም ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የግብጽ እና የሱዳንን የቅኝ ግዛት እሳቤዎች እንድትቀበል አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን የሄዱበት ርቀትና ያሳዩት ጣልቃ ገብነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ከአድዋ አኩሪ ታሪኳ ባሻገር ለቀጣናው ያላት መልክዓ ምድራዊ አቀማምጥ ወይም ጂኦ-ፖሊቲካዊ ሁናቴ ምዕራባዊያን በጫና አንበርክከው ያሻቸውን ለማድረግ ትርምስምሱ የቀይ ባህር ዳርቻ ሌላው የኢትዮጵያ ጦስ ነው። እናም ኢትዮጵያ ከጥንትም ጀምሮ የተቄመባት አገር ናት። ዛሬም ከምዕራባዊያን ጥርስ ውስጥ አልወጣችም። ዛሬም እንደሌሎች አገሮች አኝከው ካላፈራረሷት እንቅልፍ ያላቸው አይመስልም።

ከቀጥታ ወረራ እስከ የውክልና ጦርነት

የመረጃ ጦርነትና መያዶች

ምዕራባዊያን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሞክረው ካልተሳካላቸው የፊት ለፊት ቀጥታ ወረራ ወደ ውክልና ጦርነት መሸጋገር የመረጡት አንዱ መንገድ ነው። ይህም ኢትዮጵያ ጠል የሆኑ ገንጣይና አስገንጣይ ቡድኖችን መጠቀም ነው። ለዚህ ደግሞ አሸባሪው ሕወሃት ከምስረታው እስከ እርጅናው ሁነኛ መሳሪያቸው ነው። ለዚህም የተመድ ድርጅቶች በርዳታ ስም ጦር መሳሪያ አከፋፋዮች፤ የምዕራቡ ዓለም ፖሊሲ አስፈጻሚዎች ከትሕነግ ጋር ያላቸው ቁርኝት ውሎ ያደረ ነው። በተለይ ከአራት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ሽብር፣ ሰርቆት፣ ክህደት፣ ስግብግብነት፣ ወሮበልነት፣ ጥላቻና ቂም በቀልን ባህሪው ባደረገውና ገና ከጽንሱ ጀምሮ አጎልምሰው ያሳደጉት ሕወሀትን መልሶ ለማንገስ፣ ኢትዮጵያን ደግሞ ለማፈራረስ እየኳተኑ ነው።

የመረጃ ጦርነት ሌላው አገራትን የማፈራረስ መንገዳቸው ነው። ይህንንም ስልት በኢትዮጵያ ላይ ለመተግበር ስራ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ለምዕራባዊያን መንግስታት መሳሪያ የሆኑ ቡድኖችን በዓለም አቀፍ ሚዲያዎቻቸው ገጽታ ይገነባሉ። የኢትዮጵያን አንድነት የሚያቀነቅኑ ቡድኖችን ሃሳብ በማኮሰስ፣ በአንጻሩ ፀረ-ኢትዮጵያና ተገንጣይ ለሆኑ ቡድኖች ድምጽ ይሆናሉ።

በሌሎች አገራት እንዳደረጉት፣ በኢትዮጵያ ስውር ተልዕኮ ያነገቡ መያዶችንና ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን አዝምተዋል። የፕሮፓጋንዳቸው አንዱ መንስኤም ሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው። ይህ ከደርግ ዘመን የቀጠለ የአገራትን መንግስታት የማሽመድመጃ አካሄድ ነው።  

የቀድሞው የሲ.አይ.ኤ (CIA) ሰላይ ፖል ሔንዝ እና የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪቃ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ሔርማን ኮኸን ወያኔን ከደርግ ጋር ለማደራደር ያደረጉት የለንደኑ ድርድር ምዕራባዊያን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከፈጸሟቸው ታላላቅ ደባዎች ውስጥ የሚጠቀስ ነው። ዛሬም በእኛ እናደራድራችሁ ስም ምዕራባዊያን ስውር ተልዕኳቸውን የሚያስፈጽምላቸውን ቡድን ከሞት ለመታደግ ያልዞሩበት መንገድ የለም።

ኢንጋሂ ዊልያም /Engdahl, F. William/ የተባለ አሜሪካዊ ፀሐፊ ‘Manifest Destiny: Democracy as Cognitive Dissonance’ በተሰኘ መጽሃፉ የዓለም አቀፍ የነጻነት፣ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ድርጅቶች ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት ጦርነት፣ ብጥብጥና ሽብር ለመፍጠር ሲሰሩ እንድቆዩ ያትታል። እነዚህ መያዶች (መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች) በዴሞክራሲ መፈክር የዋሽንግተንን አጀንዳ የማያስፈጽሙ መንግስታትን ለማፈራረስ ስውር ዓላማ ያነገቡ እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ። ላለፉት 30 ዓመታት በላይ በዋሽንግተን የስለላ ድርጅቶችን በመጠቀም ማንኛውንም የከረረ ተቃውም ያላቸው መንግስታትን  ለማፈራረስ እንደ ቴክኒክ ተጠቅመዋል። "በ1990ዎቹ የሶቬት ሕብረት መፈረካከስ፣ የዩጎስላቪያ መበታተን፣ እንዲሁም በ1989 የከሸፈው የቻይናው ታናንሜን አደባባይ የአመጽ ሙከራ ሁነቶች በሙሉ በሲ አይ ኤና በስቴት ዲፓርትመንት የተመሩ ቅንብሮች ነበሩ” ይላል።

ስለዚህ ምዕራባዊያን አገራትን የመበታተን ገድላቸውን በኢትዮጵያ ለመድገም ካቀዱ ውለው አድረዋል።  በጂኦፖለቲክስ ፕሬስ ባለፈው ዓመት ይፋ ሆኖ የነበረው የምዕራባዊያን ድብቅ ሰነድም የባስማን ፕሮጀከት በኢትዮጵያ ለመተግበር ማቀዳቸውን ያረጋግጣል። የባስማ ፕሮጀክት/Project Basma/ በአውሮፓዊያኑ 2014 እንደ ኢትዮጵያ ጥንቷዊቷን አገር ሶሪያ ለማፈራረስ በበርካታ የእንግሊዝ-በቀል ድርጅቶች ጥምረት የተነደፈ መርሃ ግብር ነበር። ለሶሪያ ህጻናት እርዳታ ማቅረብ በሚል ሽፋን የተወጠነው ባስማ ጥንታዊቷን ሶሪያ አንኮታኩቷል። በሰብዓዊነት ካባ የጦር መሳሪያ በመጫን ለሶሪያ መንግስት ተፋላሚዎችን በማስታጠቅ ነበር ዛሬ ሶሪያ ማንነቷን እንድታጣ፣ ዜጎቿ እንዲሰደዱ፣ አገሪቷም የሃያላን ጦር ሜዳ ያደረጉት፡፡ አሜሪካ በጣልቃ ገብነት በኢራቅ፣ በሊቢያ፣ በየመን፣ በኮሪያ፣ በቬትናም፣ በላቲን አሜሪካ በሌሎችም ሀገራት አተራምሳለች፤ አገር አፍርሳለች።

ያኔ ይፋ የሆነው ኢትዮጵያን የመበተታተኛው ፕሮጀክትም “ኮማንድ ኤንድ ኮንትሮል ፊውዥን ሴንተር/Command and Control Fusion Center- C2FC/ የሚል የነበረው ሲሆን አሸባሪው ሕወሃት በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በፈጸመ በሳምንቱ እስከ አውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት የቀረበው የባስማ ሪፖርት የትግራይ ጦርነት ለኀያላን ሀገራት ሁለት ስጋቶች እንዳለው አትቷል፡፡

አውሮፓ በስደተኞች እንደሚጥለቀለቅና የኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ኤርትራ ሕብረት ለምዕራባውያን ስጋት እንዳለው ያትታል። በዚህም ቀጣናውን በማይረብሽ መንገድ ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያ መበታተን እንዳለባት ውይይት ስለመደረጉ ያብራራል፡፡ ለዚህ ተፈጻሚነት አሸባሪው ሕወሃትን ጨምሮ ሁሉም ኀይሎች የሚሳተፉበት ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት ማቋቋምና የክልሎች የመገንጠል መብት በመጠቀም በሕዝበ ውሳኔ ኢትዮጵያን ማፍረስ ግቡ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሀመድ ይህን ካልተቀበሉ እንደ ቀድሞው ዩጎዝላቪያ ፕሬዝዳንት ስሎቮዳን ሚሎሶቪች በሰብዓዊ ጥሰት ወንጀል በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት በመክሰስ አገሪቱን መበታተን አማራጭ አድርጓል። ይህ ሰነድ በወቅቱ መረጃው ቀድሞ ቢወጣም ምዕራባዊያን ግን ኢትዮጵያን የማፈራረስ ሕልማቸውን አልዘነጉም። እንደ እስስት መልካችውን እየቀያየሩ ቀጥለዋል። የትግራይን ጉዳይ እንደ ዕድል መጠቀም ላይ አሁንም ተስፋቸው እንዳልተሟጠጠ አቋም የያዙ ይመስላል። ለዚህ ማረጋገጫም ከሰሞኑ ይዘዋቸው የመጡት የሰብዓዊ መብት፣ የጦር ወንጀልና ዘር ማጥፋት አጀንዳዎች ይጠቁማሉ።

ስሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ጥናት ግብሩ ፖለቲካ የሆነ ሰሞነኛው ሰነድ  

የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ምክረ ሃሳብ ኤስ-31/1 የተሰኘው ይህ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ቡድን የተቋቋመው ባለፈው ዓመት ወርሃ ህዳር ነበር። ዓላማውም በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ገለልተኝነት ምርምራ ማድረግ እና የፍትህ ተጠያቂነት ማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጾ ነበር። ይህ ቡድን በምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት አማካኝነት ሶስት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች የተሾሙለት ሲሆን ኬኒያዊቷ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ ሰብሳቢ ሲሆኑ ስቴቨን ራትነር የተባለ አሜሪካዊ እና ራዲካ ኮማራስዋኒ ሲሪላክካዊ ዜጋ አባል ናቸው። ነገር ግን የምርመራ ቡድኑ የተቋቋመለት ስውር ዓላማ መኖሩን የጥናቱ ግኝት በግልጽ የሚያሳይ ነው።

ሰሞነኛው ሪፖርት አዲሱ የመረጃ ጦርነት አካል ነው። ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሁነኛው ግብዓት አማራጭ ነው። ሀሰተኛ መረጃ መፈብረክ፣ የኢትዮጵያዊያንን ዕውነትን በመደበቅ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ መሸወድ ነው። ይህ ሪፖርት ሁለንተናዊ መልኩና ለጥናቱ የተሄደበት መንገድ ሲፈተሽ በርግጥም ውለው ያደሩ ኢትዮጵያን የማፈራረስ የባዕዳን ስውር ተልዕኮዎች አካል እንደሆነ የሚያረጋገጥ ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ አሸባሪው ሕወሃት በቀሰቀሰው ጦርነት ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት መድረሱ ዕሙን ነው። ከዚህም ባለፈ መልከ ብዙ ግፎች፣ የጦር ወንጀልና በሰው ልጆች ላይ ሰብዓዊ መብት ጥቃቶች፣ ዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተፈጽመዋል። ማን ፈጸመው፣ የት ተፈጸመ እና እንዴት ተፈጸመ የሚለውም የችግሩ ሰለባዎች ኢትዮጵያዊያን የሚያውቁት ሐቅ ነው። ጥናት ተደረገም፤ አልተደረገም።

ያም ሆነ ይህ  በጦርነቱ ስለተፈጸሙ ሰብዓዊ መብት ወንጀሎች ገለልተኛ አካል እንዲጠና ውትወታዎች ነበሩ። በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ፈቃደኝነቱን ገልጾ፤ ዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና በኢትዮጵየ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥምር ጥምረት ትግራይን ጨምሮ በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተደረገውን ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዝርዝር ጥናት ተድረጎ ባሳለፍነው ዓመት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

ዳሩ ይህ ጥናት የምዕራባዊያን ስውር ተልዕኮ አንጋቢዎችን ፍላጎት ያላሳካ ነበር። ምክንያቱም ጥናቱ  ምዕራባዊያን በሀሰተኛ መረጃ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ለመጫን የሚሹትን አንደኛ የጦር ወንጀል ተፈጽሟል፤ ሁለተኛ መንግስት ርሀብን እንደ መሳሪያ ተጠቅሟል፣ ሶስተኛ ዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል የሚለውን ድምዳሜ እንዲያመጣ ይፈለግ ነበርና ነው።

በዚህም ከጦርነቱ መነሻ ጀምሮ ኢትዮጵያን ሲኮንኑ የነበሩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት በዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኩል ሌላ ሰብዓዊ መብትን የሚያጠና ኮሚሽን እንዲቋቀም ጥሪ አደረጉ። በምክር ቤቱ ጥሪ መሰረት ተሰብሳቢ በርካታ አገራትን የወከሉ አባላትም በሰሜን ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚያጠና ኮሚሽን እንዲቋቋም የቀረበውን ሀሳብ ተቃውመው ነበር።

ያም ሆኖ በወቅቱ ከቀረበው ሰብዓዊ መብት ጥናት ሪፖርት ይልቅ የምዕራባዊያን ስውር ፖለቲካዊ ማስፈጸጸሚያ ቡድን አቋቁሟል። ይህ የተቋቋመው ቡድንም እነዚህ ስወር ኅይላት የሚሹትን ስሁት የምርመራ ሰነድ አዘጋጅቷል። የጥናቱን ሰነዱም ውጤትም ከትናንት ጀምሮ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎቻቸው እያስተጋቡት ይገኛል። ሰብዓዊ ምክር ቤቱ በራሱ ድረ ገጽም ረቂቅ ያለውን የጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል።

የስሁት ጥናት ሪፖርቱ ስሁት መረጃዎች

የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ቡድን ያቀረበው ሪፖርት በጥቅሉ ሲፈተሽ ያልተሟላ፣ ወጥነት የሌለውና ተጨባጭነት የጎደለው ነው። የጥናት ዘዴ፣ የጥናቱ ወሰን፣ መረጃ አሰባሰብና የትንታኔ ዐውድ አንጻር ከሳይንሳዊ መንገድን ያልተከተለና ከዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ያፈነገጠ የጥናት ሰነድ ነው። በምርመራ ሪፖርት ሰበብ ፖለቲካዊ ፍላጎትን በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ለመጫን የተዘጋጀ ፖለቲካ ሰነድ እንደሆነ ያሳያል።

የቀረበው የምርመራ ሪፖርት አካሄድ ሙያዊነትና ገለልተኝነት የጎደለው፣ ወገንተኝነት ያለበት፣ እውነታን የማረጋገጥ ደረጃዎችን ያላሟላ በጥቅል የጥናት መርሆችን የሳተ ነው። ይህን ያህል ከጥናት ስልቶች፣ ትንታኔ አሰጣጥ መንገዶች፣ ከሕጋዊ የአጠናን ዐውዶች ሲታይ በርግጥም ፖለቲካዊ አጀንዳ ከማስተጋባት ዓላማ በስተቀር ይህን ሰነድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ባለሙያዎች አዘጋጁት ማለት ጥርጣሬ ይፈጥራል። ለማሳያነትም አንዳንድ ነጥቦችን መንሳት ይቻላል።

ይህ ቡድን ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል የሚል ድምዳሜ ላይ ደረስኩ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ተንቀሳቅሶ መረጃ ሰብስቦ ሳይሆን ጥቂት ግለሰቦችን ኡጋንዳ ሆኖ በበይነ መረብ አነጋገርኩ በማለትና ተጨባጭነት በሌላቸው አሉባልታዎች ላይ በመመስረት ነው። ይልቁኑም ያቀረባችው መረጃዎች በቀጥታ በምዕራባዊያን ሚዲያዎች ሲነዙ ከነበሩ ያልተሟሉ የዜና አንቀጾች ላይ በቀጥታ የተለቃቀሙ ይመስላል።

የጥናቱ መግቢያ ሲጀምርም ከአገራዊ ለውጡ እንደመጣ፣ ሕወሃት ወደ መቀሌ ሲገባ፣ በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠሩ ዘመቻዎች ሲነዙ ነበር ሲል ጥላቻውን ያስተጋባል። በሌላ በኩል አሸባሪው ቡድን አመራሮች መቀሌ ከመሄዳቸው በፊትም ሆነ መቀሌ ከመሸጉ በኋ እንደሁም ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ አስከ አሁን ድረስ ሲነዙት የነበረውን የጥላቻ ትርክት፣ በተመለከተ ያነሳው ነገር የለም። የጥናቱ ሪፖርት ከመጀመሪያው ለሕወሃት የወገነ ብቻ ሳይሆን ከሕወሃትና ደጋፊዎቹ ጋር እየመከረ ያዘጋጀው ሰነድ እንደሆነ ፍንጭ ይሰጣል።

በሌላ በኩል ገና ከጅምሩ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫው ቢራዘምም ሕወሃት የራሱን ምርጫ በማድረጉ የፌዴራል መንግስትና የትግራይ ኅይሎች እርስ በርሳቸው ‘ኢ-ሕገ መንግስታዊ ነህ’ እየተባባሉ እየተወነጃጀሉ መቀጠላቸውን በኋላም ጦርነቱ እንደፈዳ ይጠቅሳል። ይህ ማለት ጥናቱ የፌዴራል መንግስትና አሸባሪው ሕውሃትን በዕኩል ያያል ማለት ነው። እንዲሁም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የተቀሰቀሰው ጦርነት በማለት በጥናቱ መግለጽ በራሱ አሸባሪ ቡድኑ የሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ መካድ ነው። የአንድን ነገር ስረ መሰረት ማጣራት ያልቻለ ጥናት ተአማኒ ሊሆን አይችልም። በሌላ አገላለዕ የጥናቱ ቡድን አባላት አሸባሪ ቡድኑ ጦርነት መጀመሩን አያምኑበትም፤ ወይም ለመደበቅ ፈልገዋል ማለት ነው።

በሰነዱ ውስጥ ጅምላ ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ጭፍጨፋ፣ ዘር ማጥፋት የሚሉ መሰል ቃላትን ቢጠቀምም ለእነዚህ ቃላት ማስረጃው ግን የስልክ ልውውጥ መሆኑ አስገራሚ  ያደርገዋል። መቀሌ ለተደፈሩ ሴቶች ማስረጃው የህወሃት አባል የሆነን ሰው መጠየቅ ይመስላል ጥናቱ።

ይህ ቡድን በግብዓት እጥረትና መሰል ምክንያቶች የተጣለበትን ጥልቅ ምርመራ ማካሄድ እንደማይችል ቢያሳውቅም ዓላማው በኢትዮጵያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳደር ያለመ በመሆኑ የጥናት መንገዶችን ሳያሟላም ድምዳሜ ላይ የደረሰ ይመስላል። በተለይም አሸባሪው ቡድን እየተዳከመ ከመሰላቸው ሁሌ እንደሚያደርገው ሁሉ፤ አሸባሪው ሕወሃት ሶስተኛ ዙር ወራረ ፈጽሞ ወረራው እየተቀለበሰ ባለበት በዚህ ወቅት ምርመውን አወጣሁ ማለቱ ከዚህ ስውር ዓላማ ጋር የተጣጣመ ያደርገዋል። ምክንያቱም ወቅት ጠብቆ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለማሳደር የተዘጋጀ ስሁት ሰነድ በመሆኑ የጥናት ቡድኑ ላለፈው አንድ ዓመት ሲሰራ ቆይቶ ሰሞኑን ይፋ ማድረጉም፤ ይህን ዕውነታ ያስረዳል።

በሌለ በኩል ቡድኑ ከዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጽህፈት ቤትና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች የጋራ የምርመራ ሪፖርት ላይ ድክመት አለ ብሎ ካመነ ጥናቱን አሻሽሎ ማቅረብ ሲኖርበት እንደ አዲስ መጀመሩም በርግጥም ሌላ ዓላማ እንዳለው ያሳብቃል። ይህን ጥናት እነዚህን ድርጅቶች ትብብር አልተደረገልኝም ባለበት አግባብ የተሟላ ጥናት ለማቅረብ እንደማይችል ይታወቃል።

የጥናት ቡድኑ ከአዲስ አበባ ወጥቶ ወንጀሉ ወደተፈጸመባቸው ቦታዎች መሄድ እንዳልቻለ፣ የሱዳና የጅቡቲ መንግስታትም በየአገራቱ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ለማናገር ፈቃደኝነታቸውን እንዳልገለጹ ያትታል። ‘ከአዲስ አበባ አልወጣሁም፣ የጉዳት ተጠቂዎችን ማናገር አልቻልኩም‘ ቢልም እነማንና የት እንዳገኛቸው የማይታወቁ ሰዎች ደግሞ እንዳገኛቸው በደፈናው ጠቅሶ ያልፈዋል።

በትግራይ ክልል ኢንተርኔት ባለመኖሩ መረጃ ለመሰብሰብ እንዳልቻለ ቢግልጽም፣ የሕወሃትን ኅይሎችን ጨምሮ የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን በስልክ በማናገር መረጃ መሰብሰቡን ይዘረዝራል።

ቡድኑ በየትኛውም አካባቢ ባይሄድም ደደቢት ውስጥ ውስጥ ተፈናቅለው ትምህርት ቤት ውስጥ የተጠለሉ ዜጎች በድሮን ጥቃት እንደተገደሉ፣ ቦምቡም የቱርክ ድርጅት የሚያመርትው ቦምብ መሆኑን አረጋግጫለሁ ይላል። በስፍራውም ንጸሁን እንጅ ታጣቂዎች አብረው አልነበሩም ሲል በሰፍራው የተገኘ መስሎ ይደመድማል።  

በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደተዘገበውም ሪፖርቱ መንግስት የጦር ወንጀል እንደፈጸመና ርሀብን እንደጦር መሳሪያ እንደተጠቀመ የሚደመድም ነው። ከጥናቱ መቼት አንጻርም አባሪው የሕወሃት ቡድን ከታች በተዘረዘሩ ስፍራዎች የፈጸማችውን ጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች እንደሁም ከጦርነቱ መጀመሪያ ዕለት አንስቶ የፈጸማችውን የጦር ወንጀል ስር የሚያጠቃልሉ ግፎችን አላተተም። ይህም የጥናቱ ጎዶሎነትን ያሳብቃል። ይልቁኑም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትን ባልዋለባቸው ጉዳዮች ለመኮንንና ለመወንጀል ስፍራዎችና ድርጊቶችን ዘርዝሯል።

ከጥናቱ ድምዳሜዎች መካከልም በመቀሌና አካባቢው ስፋት ያላቸው ጾታዊ ጥቃቶች በመከላከያ ሰራዊት እንደተፈጸሙ ቢያትትም መረጃውን ከየትና ከነማን እንዳገኘው አይገልጽም። ያገኘው መረጃው እውነት ስለመሆኑ ያቀረባቸው የሐቅ ማረጋገጫ መንገዶችን አላቀረበም። የሚጠቅሳቸው ሐቀኛ ምስክሮች የሉተም። በሌለ በኩል መከላኪ ሰራዊት በመቀሌ የተላዩነ ተቋማት ዘርፏል በሚል በጥቅሉ ቢወነጅልም የወንጀሉን ስፋት፣ መቼ፣ እንዴት የሚለውን ተጠየቅ የሚያብራሩ መረጃዎች አላቀረበም።

በሌላ በኩል የሰብለዓዊ መብት ጥሰቶችና ወድመቶች በአማራና አፋር ክልሎችም በስፋት የተፈጸሙ ቢሆንም ይህ የጥናት ቡድን ግን ማጥናት አልፈለገም። ለማስመሰል ሲበል የጭና እና የቆቦ ጅምላ ጭፍጨፋዎችን ቢያካትትም ከደረሰው ግፍና ዘር ማጥፋት ወንጀል አኳያ በደሳሳው አልፎታል። አሸባሪውን ቡድን ወንጀሎች ለመሸፋፈን በገሃድ ወገንተኝነቱን አሳይቷል።

ይህ ጥናት ግኝት የትግራይ ታጣቂዎች በአማራ ክልል ቆቦና ጭና ንጹሃን መግዳላቸውን፣ በተወሰነ መልኩ አስገድዶ መድፈር መፈጸማቸውና ዘረፋ መፈጸማቸውን በጥቂቱ በመግለጽ ይህን ያደረጉት ግን በትግራይ ሴቶች ላይ ለተፈጸሙ ጥቃቶች አጸፋና በቀል ሲሉ ያደረጉት በሚመስል አይነት አገላለጽ በመጠቀም በዜጎች ላይ የደረሰን የከፋ በደል በንጽጽር በማቅረብ እዚህ ክልል ከተፈጸመው እዚያ ክልል የተፈጸመው አስገድዶ መድፈር የከፋ ነው በማለት በዜጎች አላግጧል።

ለምሳሌ ልክ የዛሬ ዓመት መስከረም ላይ አሸባሪው ቡድን ታጣቂዎች በአንድ ዕለት ብቻ አሸባሪው ቡድን 600 ንጹሃንን ጨፍጭፎ እንደነበር አልጀዝራ "በእስካሁኑ ጦርነት ከፍተኛውን ጭፍጫፋ በአማራ ለይ ተፈጽሟል" ሲል ዘግቦ ነበር። ሌሎች ሚዲያዎችና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መበት ተቆርቋሪዎችም 'የጅምላ መቃብሯ ከተማ' ሲሉ ጭፍጨፋውን ተቀባብለውት ነበር። በተመሳሳይ በሰሜን ጎንደር ጭና በተሰኘ ስፍራ ከ150 በላይ ንጹሃን በቡድኑ ታጣቂዎች በጅምላ መጨፍጨፋቸውን ተዘግቡ ነበር። በርካታ ስሁት መረጃዎችን ያጠራቀመው የምርመራ ቡድን ግን እነዚህን ይፋዊ ዕውነታዎች እንኳን ' ጆሮ ዳባ' ብሎ አደባብሶ አልፏቸዋል።

ዓለም አቀፉ የጸጥታው ምክር ቤት በትግራይ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ አንድ ነገር ማድረግ አለበት የሚለው የጥናት ቡድኑ ጥሪም ከጀርባው የባዕዳን ተልዕኮ ስለመኖሩ መገለጫ ነው። እንደሚታወቀው በተለያዩ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስጋት የሆኑ ዓለም አቀፋዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ሲከሰቱ የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እየገባ ይወያያል፤ ካስፈለገው የሰላም አስከባሪ ኅይል ያሰማራል። ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ አሁናዊ ሁናቴ አንጻር ከዚህ ጉዳይ ጋር የሚያገናኝ ነገር የለውም።

ጥናቱ ተፈጸሙ ስለተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎች በዝርዝርና በስፋት ማጥናት ሲገባው ምክር ቤቱ ፖለቲካዊ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት የወገንኝነት ጥሪ አስተላልፏለ። የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መላ ማበጀት ይገባዋል ሲል ጠሪ ያቀርባል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ቀደም ብሎ በዓለም አቀፉ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽህፈት ቤት እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥምር የምርመራ ሪፖርት ጥቁምታዎች መሰረት ማድረግ ያለበትን ስራዎችን ከጀመረ ሰነባብቷል። ይህም በጦርነቱ የደረሱ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ አካለት የሕግ ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚኒስትሮች የጋራ ምክር ቤተ አቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል። ረጂም ረቀት ተራምዶ  ከሰሞኑ ሪፖርት አቅርቧል። ይህ ሰሞነኛ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ቡድን የምርመራ ሰነድ ግን ዓለም አቀፍ ሕጐችን ከመጣሱ ባሻገር የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብለዓዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን ለማስፈን ያደረገውን ፈቃደኝነትና የወሰደውን እርምጃ እውቅና የነሳ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት ቀደም ብሎም ማንኛውም በገለልተኝነት ላጥና ያለ አካል ሕጋዊነትን በተከተለ አግባብ መጥቶ ማጥናት እንደሚችል ትብብር እንደሚያድርግ ፈቃደኝነቱን ገልጿል። በመጀመሪያው ጥምር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ይፋ የተደረገውን ሪፖርት በተመለከተም የጋራ ሚኒስትሮች ግብር ኅይል አቋቁሞ እርምጃ መውሰዱን ይፋ አድረጎ ነበር። ይህ ጥናት ግን የተከናወኑ የግብረ ሃይሉን ስራዎች የተመለከተበት ዕይታ የተንሸዋረረ ነው።

ኢጋድ፣ አፍሪካ ሕብረት እና የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገቡና በዓለም አቀፍ ህጎች ተጠያቂነት እንዲሰፍን በመወትወት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመድፈር ያለመ ሪፖርት ነው።  

ሶስተኛውን ዙር ጦርነት በቅርቡ የከፈተው የሕውሃት ቡድን እያለ ይህ ጥናት ግን መንግስት አሁንም ያልተገደበ ሰብዓዊ ርዳታ እቅረቦት እና ሌሎች መሰረተ ልማት ዝርጋዎታዎች እንዲከናወኑ ጥሪ ማጣጣል እንጂ ሕወሃት የሰላም እጆችን እንዲታጠፉ ማድረጉን አያወሳም።

የተካዱ ሐቆች

የጥናት ሪፖርቱ ከአጠናን ሳይንሳዊ ስነ ዘዴዎችና የትንታኔ ክሽፈቶች ባሻገር አገር ያወቃቸውን፤ ፀሐይ የሞቃቸውን እውነታዎች መካዱ አሳዛኝ ነው። የጥናቱ ዓላማ ከሰብዓዊ መብት መቆርቆር የመነጨ ሳይሆን ለፖለቲካዊ ግብ ተብሎ የተቀረበ የስውር እጆች የእጅ ጽሁፍ እንደሆነ የሚያስረዳ ሰነድ ነው።

በርካታ ቅደመ ጦርነት የተደረጉ ጉዳዮችን የጠቃቀሰው ይህ ሰነድ፤ የኢትዮጵያ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ አደረጃጀቶች ለሰላም ያደረጉትን ጥረት አላወሳም። ጦርነቱ ከጀመረ በኋላም በየጊዜው መንግስት ለሰላም ሲባል የወሰዳቸውን የሰላም አማራጮችን አላነሳም።

ሕወሃት እንደተሰደበ በቁጭት ያነሳው ይህ ጥናት አሸባሪው ቡድን ለምን በህዝብ ተጠላ፣ በስልጣን ላይ ሳለ ምን አይነት ስርዓት እንደነበር እያወቀ በታሪካዊ ዳራው ክዶታል። በርግጥ ቡድኑ ከምስራተው ጀምሮ በምዕራባዊያን ፍላጎት መኛስፈጸሚያ በመሆኑ እነዚህ አጥኚዎች ካከተቀበሉት ስውር ዓላማ በስተቀር ሕወሃትን የሚኮንን እውነታ ባያነሱ የሚገርም አይደለም።

እንደሚታወቀው መንግስት የተኩስ አቁም ውሳኔ አድርጎ ከመቀሌ በወጣ ቅጽበት አሸባሪው የሕወሃት ቡድን በቀጥታ አማራንና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ ፈጽሞ ነበር። ወራረውም 400 ኪሎሜትር ወደሌሎች ክልሎች ዘልቆ በመግባት ከሰኔ 2013 እስከ ሕዳር 2014 ድረስ ለመንፈቅ ዓመት ቆይቷል። በአማራ ክልል ብቻ ሰሜንና ደቡብ ወሎን፣ ዋግ ኸምራ፣ ደቡብና ሰሜን ጎንደርን፣ የኦሮሞ ልዩ ዞን አስስተዳድረንና ሰሜን ሸዋን ዞኖችን በፈጸመው ወረራ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል። የንብረት ውድመቱ እስከ ኅይማኖት ተቋማት ያካተተም ነበር።

ባለፈው ዓመት ከቀረቡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ሪፖርቶች በተጨማሪ መንግስት የወንጀል ተጠያቂነትን ለማስፈን ባቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል የምርመራ እና ክስ ኮሚቴ በአፋር እና አማራ ክልሎች በሚገኙ ዘጠኝ አካባቢዎች የተፈጸሙ ጥፋቶችን የምርመራ ውጤት የመጀመሪያ ምዕራፍ ረቂቅ ሪፖርቱን አውጥቷል።

በዚህም ሪፖርት በሁለቱ ክልሎች አሰቃቂ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ አማካኝነት መፈጸማቸው ተገልጿል። አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና በአፋር ክልሎች ከሕግ ውጪ 3 ሺህ 598 ንፁሃን ሰዎችን ጨፍጭፏል። እነዚህ ጅምላ ጭፍጨፋዎች ቡድኑን በጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ናቸው።

ቡድኑ በወልዲያ፣ ላሊበላ፣ ሰቆጣ፣ ጃማ፣ ወረኢሉ፣ ደሴ እና ኮምቦልቻ አካባቢዎች እንዲሁም፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እና በአፋር ክልል በአውሮጳዊያን ዘመን አቆጣጠር  ከመስከረም 15 እስከ ጥር 31 ቀን 2021 ድረስ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ የጣሱ በጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ በርካታ ጥፋቶችን በአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ስለመፈጸማቸው አረጋገጧል።

በዚህም ከሕግ ውጪ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 3 ሺህ 598፤ አካል ጉዳት የተዳረጉ 1 ሺህ 315 ሰዎች ሲሆኑ 2 ሺህ 212 ሴቶች ደግሞ አስገድድ መድፈር ተፈጽሞባቸዋል። ከ452 በላይ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጥሷል የሚል ነው።

ከሕግ ውጪ በሕወሃት ግድያ ከተፈጸመባቸው መካከልም በወልዲያ እና አካባቢው ብቻ 1 ሺህ 181 ሰዎች፣ በሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች በህወሓት እና ሸኔ ሽብር ቡድኖች በሰሜን ሸዋ ዞን 257 ሰዎች፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ 162 ሰዎች በግፍ ተገድለዋል። እነዚህ ቁጥሮች ግን አሸባሪውን ቡድን ለሚደግፉ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጥኚዎች ምንም ይመስላሉ።

የትግራይ ሴቶች የኢትዮጵያና የኤርትራ ሃይሎች እንደሁም በፋኖ ሃይሎች ሰብዓዊ ክብንራቸውን በሚያወርዱ ስድቦች እየተሰደቡ ተደፍረዋል የሚለው ይህ ሪፖርት በአማራና አፋር ክልል የተፈጸሙ አስገድዶ ደፈራዎችና ጾታዊ ጥቃቶችን እምብዛም ነው ብሎ አልፎታል። የአሸባሪው የሕወሃት ቡድ ከህጻናት እስከ መነኩሴዎች ለሰሚ ጆሮ በሚሰቀጥጥ ሁኔታ የቡድን አስገድዶ መድፈሮችን በየስፍራው መፈጸማቸው የአደባባይ ሐቅ ቢሆንም ይህ ዕውነታ ተክዷል።

በሌላ በኩል በአፋር ክልል ከፍተኛ ጥፋት ያደረሰው አሸባሪው ህወሓት የ263 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ዳሩ ግን ይህ የምርመራ ሪፖረት እነዚህን እውነታዎች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማድረስ አልፈለገም። አሸባሪው ቡድን ከንጹሃን ጭፍጨፋ ባሻገርም በሰው ልጆች ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችና የጦር ወንጀሎችን ማንሳል አልፈለገም።

የመንግስት ወታደሮች በትግራይ ክልል መቀሌ ወስጥ በተቋማት ለይ ዘረፋ ፈጽመዋል ያልው ሪፖርት  አሸባሪው ቡድን ወረራ በፈጸመባቸው የአማራና አፋረ ክልሎች ሁለንታነዊ ውድመቶችን ብቻ ሳይሆን በትግራይ ክልል ያወደማቸውን አየር ማረፊያዎች፣ ድልድዮችና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ጉዳይ አላነሳም። አሸባሪው ቡድን ለሰብዓዊ ርዳታ የገቡ የዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት ንብረቶችን (ነዳጅን ጨምሮ) መዝረፉን  ክዷል።

መንግስት በትግራይ ክልል መሰረተ ልማት እንዲቋረጥ አድርጓል ሲል የኮነነው ሪፖርቱ፤ በትግራይ ክልል ከ100 ቢሊየን ብር በላይ ወጭ አድርጎ ያከናወነውን መልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ስራዎች እውቅና መስጠት ቀርቶ ክዶታል።

መንግስት ርሀብን እንደ ጦር መሳሪያ እንደተጠቀመ የሚያትተው ይህ ስሁት ሰነድ በአንጻሩ መንግስት በተናጠልም ሆነ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ያደረገውን ሰብዓዊ ርዳታ አቅርቦት ክዷል። መንግስት ጦርነቱ ከተጀመረ ጀምሮ በክልሉ ከሚገኙ 92 ወረዳዎች መካከል በ78ቱ ሰብዓዊ ርዳታ እንዲደርስ ያደረገ ሲሆን ከነዚህም መካከል ከ5 ነጥብ 8 ሚሊየን ሰዎች ተጠቃሚ አድርግል። ከቀረበው ሰብዓዊ ርዳታ መካከልም የኢትዮጵያ መንግስት 70 በመቶ ቀሪው ደግሞ በዓለም አቀፍ አጋሮች የተሸፈ ነበር። ይህ ዕውነት ግን ተደብቋል። በሌላ በኩል አሸባሪው ቡድን ሰብዓዊ ርዳታ እንዳይደርስ በተደጋጋሚ ማስተጓጎሉን በማለፍ ክህደቱን አሳይቷል።

ምዕራባዊያን ሰብዓዊ መብት ጥሰት አይገዳቸውም!

በርግጥ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት የጥቂቶች ኅያላን ምዕራባዊያን ፍላጎት ማስፈጸሚያ ናቸው። አገራትን እንደፈለጉ የሚያሾሩበት፣ ሶስተኛው ዓለም አገራትን እንዳሻቸው የሚዘውሩበትና የሚበዘብዙባቸው ድርጅቶች ናቸው። የእስካሁን ታሪካቸውም የሚያስረዳው ይህንን እውነታ ነው። ግባቸው የሉዓላዊ አገርን መድፈሪያ መሳሪያዎች ናቸው።

በሕወሃት የ27 ዘመነ መንግስት ያልተፈጸሙ መንግስታዊ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎች በነዚህ አካላት አልተጠኑም። በደርግን ዘመን በትግራይ ተፈጸመ እያሉ ሲያወጧቸውን የነበሩ ሪፖርቶችን አሸባሪው ሕወሃት ግና ጫካ እያለ ከህዝብ የመጣን ዕርዳታ ሽጦ መሳሪያ ሲገዛ፣ ህዝቡም በርሀብ ሲያልቅ ያሉት ነገር አልነበረም። ሕወሃት ግና ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በአርባጉጉና በሌሎች አካባቢዎች በአማራ ማንነት ባላቸው ዜጎች ላይ ለደረሰው ዘር ጭፍጨፋ አምነስቲ ኢንተርናልን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነን የሚሉ የምዕራባዊያን ድርጅቶች በሰነድ ተዘጋጅቶ ቀርቦላቸው አናምንም በማለት ውድቅ አድርገዋል።

አሸባሪው ሕወሃት ከማዕከላዊ መንግስትነት በሕዝብ ተገፍቶ መቀሌ ከከተመበት 2010 ጀምሮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመላው ኢትዮጵያ ያደረሳቸውን ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ ጅምላ ግድያዎች፣ ስነ ልቦናዊና አካላዊ ጉዳቶች የንብረት ውድመቶች... አንድም ጊዜ አሳስቧቸው ሪፖርት አቅርበው አያውቁም።

ይሕ የሽብር ቡድን በይፋ አገራዊ ጦርነት ከመቀስቀሱ ቀደም ብሎም በመቀሌና በሌሎች የትግራይ ከተሞች በሽብር ቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች የሚፈጸሙ አስገድዶ መድፈር ጥቃቶችን በመቃወም በክልሉ የተደረጉ የሴቶች ሰልፎችን ከቁብ አልቆጠሯቸውም። ቡድኑ የምዕራባዊያን ጸረ ኢትዮጵያ አቋም ማስፈጸሚያ እስከሆነ ድረስ በቡድኑ የሚፈጸሙ ፆታዊ ጥቃቶችና ወንጀሎች ለዜና የሚበቁ አልነበሩም።

አሸባሪው የሕወሃት ቡድን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የአገሪቷን መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ በመጨፍጨፍ ወደ ስልጣን ለመመለስ ሙሉ ወረራ ሲያድረግ ያሉት ነገር አልነበረም። በሌላ በኩል የአገር ሉዓላዊነትን ከደፈረ አሸባሪ ቡድን ጋር ታረቁ ማለት ጀማምሩ። በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የጸጥታ ሃይል ስምሪት ላይም በጣልቃገብነት ተዳጋገሚ መግለጫዎች ሲሰጡ ነበር። በሌላ በኩል የሽብር ብድኑ አገር የማፍረስ ዕኩይ ዓላማ ከሽፎ ሰራዊቱነ ትግራይን ሲቆጣጠርና የሽብር ቡድኑ መሪዎች ጉድጓድ ለጉድጓድ ሲሸሹ፣ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ የመሰሉ ወገኖች መከላከያ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽማል የሚል ስጋት እንዳላቸው ፕሮፓጋንዳ መንዛት ጀመሩ።

በኋላም መንግስት የተኩስ አቁም ማድረጉን ተከትሎ መከላከያ ሰራዊት መቀሌን ለቆ ከወጣ በኃላ አሸባሪው የሕወሃት ቡድን የሕዝቡን ስቃይ አብዝቶቷል፤ ሰብዓዊ እርዳታ በማስተጓጎል ሰብዓዊ ቀውስ እንዲደርስ አድርጓል። ግፍና በደል አክፍቷል። ሕጻናትና አቅመ ደካሞችን ወደሌላ ጦርነት አሰልፏል። መሰረተ ልማቶችን አውድሟል። የአማራና አፋር አጎራባች ክልሎችን በመውረር ጥቃትና ዝርፊያ ፈጽመዋል፤ ከግማሽ ሚሊየን የላነሰ ህዝብ አፈናቅሏል።

የቡድኑ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የሚፈጽማቸው ድርጊቶች በዓለም አቀፍ የጦር ወንጀለኝነትና በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠይቁ ቢሆንም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ግን በተቃራኒው ጎራ ተሰልፎ ኢትዮጵያን የማፍረስ ስራ ተጠምዶ ነበር።  

ማይካድራን ጨምሮ በሌሎች ሲፈጽም ዘር ማጥፋት ሲፈፅም፣ ህጻናትን ለጦርነት ሲያሰልፍ በዝምታ የማለፋቸው ምስጢርም መነሻቸው ለዴሞክራሲና ሠብዓዊ መብት በመቆርቆር ሳይሆን ለአሜሪካ መንግስት ተላላኪ የሚሆን ስርዓት ለመፍጠር በማለም ነው።

የአጥኚ ብድኑ ስብጥር 'እሾህን በእሾህ'

ሰሞነኛው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሪፖርት አዘገጃጀት ኮሚቴ አባላት ስብጥር የራሱ መልክ ያለው ይመስላል። የጥናቱ ቡድን ሰብሳቢ ካሪቬቲ የጎረቤት ኬኒያዊት መደረጓና ሌላውም አባል ሲሪላንካዊ መደረጉ፣ አጥኚዎች ኡጋንዳ ውስጥ መሽገው ጥናት ያሉትን ስውር ተልዕኮ ያነገበ ስሁት ሪፖርት ያቀረቡበት መንገድ እሾህን በእሾህ ነው ጉዳዩ። ሪፖርቱንም ገለልተኛ ለማስመሰል ያለመ ሴራ ይመስላል ነው።

'የአፍሪካን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል' የሚለውን እሳቤ የማይወዱት ምዕራባዊያን የአፍሪካን አገራት በአፍሪካዊያን ልሂቃን ችግር ውስጥ መክተት በሚለው 'የእሾህን በእኞህ' ስልትን ይከተላሉ።

የወያኔ ስርዓት የሚያስፈጽመው በእነርሱ ጥቅምና ጥያቄ የተቃኘ ዕቅድና ፕሮግራም ነበረው። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረው የልማት እንስቀስቃሴ በተለይም በምግብ ራስን የመቻል ንቅናቄና የሜጋ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ኢትዮጵያና መሰሎቿን በድህነት አረንቋ ውስጥ ሳይወጡ የምዕራባዊያን ዕጆች እየጠበቁ እንዲኖሩ ለሚሹ ወገኖች ራስ ምታት ነው። ስለዚህ እርስ በርስ ማናቆር፣ ውስጣዊ ሽኩቻ ማፋፋም አዋጭ መንገድ ሆኖ ተወስዷል። በኢትዮጵያ ተገንጣይ ቡድኖችን የመደገፉም ምስጢርም ይሄው ነው። የምዕራቡ ዓለም ጫና ማብዛት ተላላኪና ዓላማቸውን የሚያስፈጽም የኢትዮጵያ መንግስት እንዲፈጠር ከመሻት የመነጨ እንደሆነ ይታወቃልና።

በሌላ በኩል አገራትን በአገራት ላይ ላይ እንዲነሱ የማድረግ ፖለቲካዊ የዲፕሎማሲ አካሄዶችም የዚህ አካል ናችው። ታላቁ የኢትዮጵየ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በተለያየዩ የተፈጥሮ ሀብቶች በጋራ ከመልማት ይልቅ ወደ እርስ በርስ ስጋት መተያየትና ጥል እንዲገቡ ይሰራሉ። ኢትዮጵያ ከወዳጅ ጎረቤቶቿ ጋር እንዲጣሉ የማድረግም አንዱ አካሄድ ነው። ይህ በርግጥም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት ጀምረው በሰፋት የሰሩት ዕውነታ ነው። የጥናቱ ቡድን አባላት ማንነትም በርግጥም ከዚህ ጋር የራሱ አንድምታ እንዳለው መገመት ይቻላል።  ይህን አገራትና መሪዎች ልብ ካላሉ በአንዳንድ ምዕራባዊያን የተሸረበላቸው ሴራ ውስጥ መግባታቸው ስለማይቀር በጥንቃቄ ማየት ይሻል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም