የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቀቆ ለአገልግሎት በቃ

ዲላ መስከረም 11/2014 (ኢዜአ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ በ18 ሚሊዮን ብር ወጭ ያስገነባው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ ።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ ተጠናቆ ሥራ መጀመር በከተማው የትምህርት ተደራሽነትን ከማስፋት ባለፈ ጥራትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ተመላክቷል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ዓለሙ የትምህርት ቤቱ ግንባታ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

ይህም በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ትምህርት ቤት የሚስተዋለውን የመማሪያ ክፍሎች እጥረት ሙሉ በሙሉ ከመቅረፉ ባለፈ በከተማው የትምህርት ተደራሽነትን እንደሚያሰፋም ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱ በአራት ህንጻዎች 20 የመማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ ቤተ መጻህፍት፣ መፀዳጃና መታጠቢያ፣ የአስተዳደር ቢሮ፣ የመምህራን ማረፍያና ሌሎች ተያያዥ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑንም አስረድተዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቱ ባጠቃላይ ከ1 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ያለው ሲሆን ለግንባታውም 18 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉንም ጠቅሰዋል።

ዩኒቨረሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ሰራተኛውንና የአከባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት እያደረጋቸው ከሚገኙ ስራዎች  አንዱ ትምህርት መሆኑን ጠቅሶ ይህም ተጠናክሮ እንደምቀጥል ነው የጠቆሙት ።

ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ትምህርት ቤት በማቋቋም ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ባሉት የትምህርት እርከኖች 1 ሺህ 400 ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የትምህርት ቤቱ ስራ አስኪያጅ መምህርት እመቤት ተክሌ ናቸው።

ዩኒቨርስቲው ያስገነባው አዲስ ህንጻ ወደ ሥራ መግባቱ የትምህርት ቤቱን የመበቀል አቅም ከማሳደግ ባለፈ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል እንዲሁም ግቢው ለተማሪዎችና መምህራን ምቹ እንዲሆን ጉልህ አስተዋጾ እንዳለው ጠቅሰዋል።

ከተማሪ ወላጆች መካከል ወይዘሮ ዘውዲቱ ብርሃኑ በበኩላቸው ትምህርት ቤቱ የተሻለ ጥራት ያለው ትምህርት ለአከባቢውና ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል።

አዲሱ ህንጻ ተገንብቶ ወደ ስራ መግባቱ ደግሞ ከዚህ ቀደም በመማሪያ ክፍሎች እጥረት አገልግሎቱን ያላገኙ አካላት እድል እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም