ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ አሉታዊ መረጃ የሚያሰራጩ አፍሪካዊያን ጋዜጠኞች በአህጉሪቷ ህዝብ ላይ እንደዘመቱ እንቆጥረዋለን- ኡጋንዳዊ ጋዜጠኛ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ አሉታዊ መረጃ የሚያሰራጩ አፍሪካዊያን ጋዜጠኞች በአህጉሪቷ ህዝብ ላይ እንደዘመቱ እንቆጥረዋለን- ኡጋንዳዊ ጋዜጠኛ
መስከረም 11/2015 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ የተሳሳተና አሉታዊ መረጃ የሚያሰራጩ አፍሪካዊያን ጋዜጠኞች በአህጉሪቷ ህዝብ ላይ እንደዘመቱ ሊገነዘቡት ይገባል ሲል ኡጋንዳዊው ጋዜጠኛ ኩንጉ አልማህዲ አዳም ተናገረ።
ከታዋቂ የኡጋንዳ መገናኛ ብዙሃን አንዱ የሆነው የ'ኒውስ ፕላስ ኡጋንዳ' ማኔጂንግ ኤዲተር ኩንጉ አልማህዲ አዳም፤ ኢትዮጵያን የተመለከቱ ጉዳዮችን በመተንተን ይታወቃል።
ከሚጽፍባቸው ጉዳዮች አንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን የተመለከተ ሲሆን ጋዜጠኛው ከሰሞኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሮጀክቱን በአካል ጎብኝቷል።
'ይህ ድንቅ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላ ፍሪካ ትልቅ ተስፋ የሰነቀ ፕሮጀክት ነው' የሚለው ጋዜጠኛው በጉብኝቱ መደሰቱን ተናግሯል።
የመጎብኘት አድል በማግኘቱም ስለግድቡ በስፋት የጻፈባቸውን ዕውነታዎች እንዲያረጋግጥ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረለት ገልጿል።
የኅይል ማመንጫ ግድቦች በውሃው ሃይል ከማመንጨት በስተቀር ውሃን የሚያስቀሩ አይደሉም የሚለው ጋዜጠኛው፤ በታችኛው ተፋስስ ያሉ ወገኖች ይህን እውነታ መገንዘብ እንደሚገባቸው ተናግሯል።
በቀጣይም ስለ ኢትዮጵያ ያሉ ዕውነታዎችን በሚዲያ መሞገቱን እንደሚቀጥል አረጋግጦ፤ በፕሮጀክቱ ላይ ያደረገው ጉብኝትም ተጫማሪ ግብዓት እንደሚሆነው ገልጿል።
የተቀሩ የአፍሪካ ጋዜጠኞችም ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውነታዎችን በማረጋገጥ በተቃራኒው የሚነዙ ሀሰተኛ ትርክቶችን በማጋለጥ ሊሰሩ ይገባል ነው ያለው።
ግድቡ ለመላው አፍሪካዊያን የጋራ ተጠቃሚነት ተስፋ የሰነቀ መሆኑን የሚናገረው ጋዜጠኛው በሀሰት የሚዘምቱ አፍሪካዊያን ጋዜጠኞች በአፍሪካ ህዝብ ላይ የጥፋት ዘመቻ እያካሄዱ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብሏል።
ብዙ ቢሊየን ሀብት እየፈሰሰበት ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግደብ በኢትዮጵያዊያን አቅም እንጂ በውጭ እጅ ድጋፍ የሚገነባ አለመሆኑም የተቀረው አፍሪካ ከኢትዮጵያ ትምህርት ሊወስድ ይገባል ባይ ነው።
በሕይወቴ ከኢትዮጵያ ውጭ እንዲህ መሰል ትልቅና አስተማማኝ የፕሮጀክት ስኬት አላየሁም ሲልም ተናግሯል።