የትግራይ ክልልን መልሶ ለማቋቋም በመንግስት የተከፈለው ዋጋና የውጭ ኃይሎች "የተንሸዋረረ" እይታ

19

መስከረም 11/2015 (ኢዜአ)፡ የትግራይ ክልልን ህዝብ መልሶ ለማቋቋም በመንግስት የተከፈለው ዋጋና የውጭ ኃይሎች "የተንሸዋረረ" እይታ

የደቀቀ ማህበረሰብና ምጣኔ ሀብት፣ የማያባራ ግጭትና ጦርነት፣ ያልተረጋጋ መንግስትና የተዳከመች ሀገር መፍጠር የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ያልተቋረጠ ህልም ነው።

ለዚህ ደግሞ "የጡት ነካሹ" አሸባሪው ህወሃት ከትጥቅ ትግል እስከ መንግስት፤ ከመንግስትነት ደግሞ እስከ ሽብር ቡድን በዘለቀው ጉዞው ሀገርን የማዳከም ቃለመሃላውን እየተወጣ ነው።

አንዳንድ የውጭ ኃይሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማትን ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጭ በመጠቀም ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳረፍ ብዙ ጥረዋል።

ሰሞኑንም በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የተቋቋመው የጥናት ኮሚሽን ኢትዮጵያን "በቁስሏ ላይ እንጨት በመስደድ፣ ጡት ነካሿን አወድሶ፣ ጫና ለማሳረፍ የሚከጅል ስሁት ሪፖርት" አቅርቧል።

የፌደራሉ መንግስት የተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ መውጣቱን አስቀድሞ መረጃ ባላቸው ባለሙያዎች የተዘጋጀው ሰነድ መንግስትን "ኤሌክትሪክሲቲ፣ ኢንተርኔትና ሌሎች የቴሌኮም እና የባንክ አገልግሎቶችን አቋርጧል" ሲል ይከስሳል።

በዚህ የስውር ኃይሎችን ፖለቲካዊ ግብ ባነገበ መረጃ ውስጥ ግን ለግባቸው አመቺነት ሲባል አሸባሪው ህወሃት አለሁልህ በሚለው የትግራይ ህዝብ ላይ መፃዒ ተስፋውን የሚያኮሰምን ወንጀል መፈጸሙ አልተካተተም።

አሸባሪው ህወሃት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ መንግስት የጀመረውን የህግ ማስከበር እርምጃ ተከትሎ የሽብር ቡድኑ ኢትዮጵያ ከድሃ መቀነቷ አውጥታ የገነባቻቸውን መሰረተ ልማቶች አውድሟል።

የሀገርና የህዝብ ሀብትን መዝረፍ ልማዱ የሆነው ይህ ቡድን፤ መሸሸጊያ ያደረገውን የትግራይ ክልል ህዝብ ብሩህ ቀኖች ነጥቆ በጨለማ እንዲንፏቀቅ እያስገደደው ይገኛል።

ለአብነትም የአክሱምን አውሮፕላን ማረፊያ በከባድ መሳሪያዎች አፈራርሷል፤  የቴሌኮም አገልግሎት ሰርቨሮችን ዘርፏል አውድሟል፤ ይህንን ሲፈጽምም በስውር ካሜራ መቀዳቱን ልብ ይሏል።

የትግራይ ክልል ህዝብ የሚገለገልባቸውን የንዋይ ተቋማት ካዝና ሰባብሮ ገንዘቡን ወደ ኪሱ ህንጻዎችን ደግሞ ወደ አመድ ቀይሯል።

የተከዜ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን የኃይል ማከፋፈያ ማሺኖች በከባድ መሳሪያ በመምታት ህዝብ በጨለማ እንዲኖር ማስገደዱም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት ህሙማን የሚረዱባቸውን የጤና ተቋማት፣ ትውልዱ የሚማርባቸውን ትምህርት ቤቶች ዘርፏል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዓይኖች የሽብር ቡድኑን ዕኩይ ተግባር ቢመለከቱም እንዳላዩ አልፈውታል።

አሁን የወጣው ስመ ኮሚሽን ሪፖርትም "ዓይኔን ግንባር ያድርገው" በሚል የሰመረተ ልማት ቀበኛው አሸባሪው ህወሃት የፈጸማቸውን ውድመቶች በዶሴው አልከተበም።

የፌደራል መንግስቱ ለወራት በወሰዳቸው የተቀናጁ እርምጃዎች የሽብር ቡድኑን በማዳከም በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሞ ህዝቡ ወደ መደበኛ ህይወቱ እንዲመለስ ብዙ ጥሯል።

አሸባሪው ያጨለመውን የትግራይ ክልል የነዋሪውን ተስፋ የሚያለመልሙ መሰረታዊ አገልግሎቶችን አስጀምሯል።

የወቅቱ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር  የነበሩት የአሁኑ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ የሚያነሱት ይህንኑ ነው

በዚህም ለትግራይ መልሶ ግንባታ በ2013 ዓ.ም ስምንት ወራት ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ፈሰስ ተደርጓል።

ሆኖም በትክክል መመልከት ያለቻሉት (ባለ ሸውራራ ዓይኖቹ) አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ምዕራባውያን ሀገራት የመንግስትን በጎ ርምጃዎች ከቁብ አልቆጠሯቸውም።

የፌደራል መንግስቱ ቀጥሎም ለትግራይ ክልል ህዝብ በሰላም ወጥቶ መግባትና አርሶ መብላት ሲል ሰራዊቱን ከትግራይ ክልል አስወጣ።

ይህንን እንደ እድል የተጠቀመውና "አይጥ ጉድጓድ" ውስጥ ተደብቆ የሰነባበተው የሽብር ቡድኑ ሃይል ከየተደበቀበት ዋሻ በመሰባሰብ ዳግም ጦርነት ከፍቷል፤በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ለወራት በፈጸመው ወረራም የሰው ልጅን ሞራል የሚጻረሩ ግፎችን ፈጽሟል።

የአማራ ክልል ባወጣው መረጃ መሰረትም በሰዎች ላይ ከፈጸመው ግፍ ባሻገር 288 ቢሊዮን ብር የሚገመት የቁሳዊ ሀብት ውድመት ፈጽሟል።

በዚህም ወረራ በተፈጸመባቸው ባንኮች፣ የውሃ፣ የቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ፣ የጤና፣ የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።

የአፋር ክልልም በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመቱ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መውደማቸውን መግለጹ ይታወሳል።

አሸባሪው ህወሃት ይህንን ሁሉ ሲፈጽም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብና የፕሮፓጋንዳ ማሺኖቻቸው ዝም ጭጭ ብለው አልፈውታል።

ዓይናቸውን "በጨው አጥበውና አንሸዋርረው" ለፖለቲካዊ ግባቸው አመቺነት ሲባል ፖለቲካዊ ሰነዳቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት የጥናት ሪፖርት በሚል ትናንት ይፋ አድርገዋል።

የኮሚሽኑ ሰነድ ለአሸባሪው ህወሃት የፅድቅ መንገድን ሲተልም የፌደራል መንግስቱን ጫና ውስጥ የማስገባትና በጎ ጥረቶቹን የማጣጣል ሂደት ቀጣይነትን አሳይቷል።

ለአብነትም የፌደራል መንግስቱ የትግራይ ክልልን ለቅቆ በመውጣት የተኩስ አቁም አድርጎ ሳለ በሰነዱ ግን የፌደራሉ መንግስት ኤሌክተሪክሲቲ፣ ኢንተርኔትና ሌሎች የቴሌኮምና የባንክ አገልግሎቶችን መዝጋቱን  በማንሳት በስማ በለው ይከስሳል።

አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ ውጊያ በከፈተበት ማግስት የወጣው ሰነድ የኢትዮጵያን ሀቆች ክዶ የተጋላቢውን የሽብር ቡድን የሀሰት ትርክቶች አጋንኗል።

በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥናት ኮሚሽን ስም ቢወጣም አንዳንድ የውጭ ሃይሎች የመንግስታት ተቋማትን ከመርህ ውጭ እንደሚጠቀሙባቸው ፖለቲካዊ ሰነዱ በተዛነፉ መረጃዎቹ አሳብቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከዚህ ቀደም አሸባሪው ህወሃት ለማዳን የሚደረገው የማያባራ ጩኸት መነሻው አንዳንድ የውጭ ሃይሎች ከራሳቸው ዓላማ አንጻር የሚያራምዱት "የተንሸዋረረ አቋም" ነው ሲሉ መግለፃቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም