የኢትዮጵያ ቡና በጥራት፣ በተወዳዳሪነትና በዋጋ አስደናቂ ውጤት እየተመዘገበበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ቡና በጥራት፣ በተወዳዳሪነትና በዋጋ አስደናቂ ውጤት እየተመዘገበበት ነው
መስከረም 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቡና በካፕ ኦፍ ኤክስለንስ በጥራት፣ በተወዳዳሪነትና በዋጋ አስደናቂ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን በኢትዮጵያ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንሲ አስተባባሪ ገለጹ።
በመጀመሪያውና ሁለተኛው የባለ ልዩ ጣዕም /የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ/ ውድድር የኢትዮጵያ አስደናቂ ውጤት የተገኘበት መሆኑ ይታወቃል።
የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ሶስተኛው ውድድር የቡና እና ሻይ ባለስልጣን ከአሊያንስ ኮፊ ኤክሰለንስና ዩ ኤስ ኤይድ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን የኢትዮጵያ ቡና አሸናፊ ሆኗል።
በኦንላይን ጨረታ በተከናወነው መርሃ ግብር አንድ ኪሎ ቡና 884 ሳንቲም 10 ዶላር ወይም 47 ሺህ 236 ሳንቲም 23 ብር ለመሸጥ ችሏል።
በዚህም የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር የኢትዮጵያ ጥራቱ የተጠበቀ ቡና ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ ይነገራል።
በባለፈው አመት በተካሄደው ውድድር ከ22 አገራት 170 ገዥዎች ተመዝግበው የኢትዮጵያን ቡና ለ11 ሰአታት በመጫረት አንድ ኪሎ ግራም ቡና 47 ሺህ 236 ነጥብ 23 ብር ተሽጧል።
በኢትዮጵያ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንሲ አስተባባሪ ቅድስት ሙሉጌታ፤ የኢትዮጵያ ቡና በውድድሩ በሁሉም መልኩ የዓለምን ቀልብ እየገዛ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ቡና በካፕ ኦፍ አከስለንስ በጥራት፣ በተወዳዳሪነትና በዋጋ አስደናቂ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን ነው የተናገሩት።
በካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ መሳተፍ የቡና ገዥዎች የውድድሩ አሸናፊ የሆነው አምራች አርሶ አደር ወደ ሚገኝበት አካባቢ ሄደው እንዲያበረታቱና ሌሎችም ተጠቃሚ እንድሆኑ አድል የሚያመቻች ነው ብለዋል።
በሦስተኛውን ዙር ውድድድር አሸናፊ የሆኑት አርሶ አደር ለገሠ በጦሳ፤ 1 ኪሎ ግራም ቡና 47 ሺህ 236 ብር በመሸጥ በድምሩ 479 ኪሎ ግራም 22 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር መሸጥ ችለዋል።
ከ23 አገራት የተወጣጡ 170 ገዢዎች ተሳታፊ በሆኑበት የዘንድሮው በውድድር ማሸነፍ የቻሉት በአነስተኛ ማሳ ላይ ጥራቱን የተጠበቀ ቡና አምርተው በማቅረባቸው ሲሆን የቡናው ዋጋም የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ሽያጭ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
የካፕ ኦፍ ኤክሰለስ የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ውድድር ናሙና መቀበያ በጅማ፣ በሃዋሳና በድሬዳዋ ከተሞች መኖራቸው ይታወቃል።
የቡና ጥራት ውድድር ባለፉት 20 ዓመታት በተለያዩ የአለም አገራት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በኢትዮጵያ ሲካሄድ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
በ2014 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከውጪ ንግድ ካገኘችው 4 ነጥብ 12 ቢሊየን ዶላር 1 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላሩ ከቡና የተገኘ መሆኑ ይታወቃል።
በ2015 በጀት ዓመትም 360 ሺህ ቶን ቡና ለውጪ ገበያ በማቅረብ 2 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት የታቀደ ሲሆን ሌሎች ምርቶችንም ጨምሮ በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ 5 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል።