ቀጥታ፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአገዛዝ ዘመኑ የኦሮሞን ህዝብ ሀብት ከመዝረፍ አልፎ የመብት ጥያቄ ሲያፍንና ሲገድል የነበረው ቁስል አልዳነም- የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት

መስከረም 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአገዛዝ ዘመኑ የኦሮሞን ህዝብ ሀብት ከመዝረፍ አልፎ የመብት ጥያቄ ሲያፍንና ሲገድል የነበረው ቁስል አልዳነም ሲሉ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ገለጹ።

የህብረቱ አባላት እንደገለጹት አሸባሪው ቡድን የኦሮሞ ህዝብ በማንነቱ ቀና ብሎ እንዳይሄድና ባህሉን እንዳያሳድግ በማድረግ የማደከም ስራ ሲሰራ ነበር።

በ2009 ዓ.ም በሆራ አርሰዲ በነበረው የኢሬቻ በዓል ስነ ስርዓት ለማክበር በተሰበሰበው ህዝብ ላይ ጥቃት በመፈፀም ከአንድ ቤተሰብ እስከ አምስት የሚደርሱ ልጆች ያቁበት ክስተት የቡድኑ የጥፋት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ 27 ዓመት ሙሉ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ፣በኦሮሞ ቄሮና ቀሬዎች ብሎም የኦሮሞ ምሁራን ላይ ይሄ ነው የማይባል ግፍ ሲፈፅም የኖረ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ጀግና ወጣቶችን የበላ ቡድን ነው ያሉት አባገዳዎች በ27 አመት የአገዛዝ ዘመኑ የመሬት፣የገንዘብና የንብረት ዝርፊያ ሲፈጽም ነበር።

አሸባሪው ቡድን በአገዛዝ ዘመኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ከስልጣን እስከተወገደበት ጊዜ ድረስ ህዝብ እና ሃገር ላይ ከፍተኛ በደል አድርሷል።

ቡድኑ ወደ ስልጣን ሲመጣ ለኦሮሞ ህዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ አስቦ አይደለም የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ መሆኑን የገለጹት አባገዳዎቹ ይህ ድርጊቱ ህዝቡን የመረረ ትግል ውስጥ እንዲገባ ማድረጉንም ተናግረዋል።

የትግራይ ህዝብ ከኦሮሞ ህዝብና ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ጋር ቢኖር ይሻለዋል ያሉ ሲሆን አሸባሪው ቡድን ህዝቡን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየወሰደው ነው ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ ለጥቂት ግለሰቦችና ቡድን ጥቅም ሲባል ልጆቹን ያልተፈለገ ዋጋ ባያስከፍል እንደሚሻል ገልጸዋል።

ሰላም ሲኖር ልማትና እድገት ይኖራል ፤ሰላም የነሳንን አሸባሪውን ቡድን እናወግዛለን ያሉት የኦሮሞ አባገዳ ህብረት አባላት፤ አሸባሪው ቡድን በአሁኑ ሰዓትም የሰላም ጠል በመሆን ጦርነት መክፈቱን ለውጪው ማህበረሰብ ማስገንዘብ ይገባል ብለዋል።

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የከፈተውን ጦርነት እየመከተ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚደረገው ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት ገልጸው፤የኦሮሞ ህዝብም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ብቸኛ ሃገሩን በአንድነት መጠበቅ አለብን ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም